በዲያቆን ሔኖክ ኃይሌ
ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በይፋ ጉባኤያትን አቁማለች:: የነፍስ ሕይወት መድኃኒት የሆነ ሥጋ ወደሙን ለመቀበል በምንገኝበት ቅዳሴና በጸሎተ ዕጣን ጊዜ ደግሞ ከማኅበራዊ ፈቀቅታ ጋር በጥንቃቄ እንድናደርግ እና ከአባቶች ጋር በቅርበት የሚሠሩ የጤና ባለሙያዎችን ምክር እንድንሰማ አሳስባለች:: ይህንን የጥቂት ጊዜ ዕድልም ብንሞትም ብንኖርም ለክርስቶስ የሚያደርገንን ጸጋ ለማግኘት ለንስሓና ለቁርባን እንጠቀምበት:: “ማንም ሊሠራባት ከማይችልባት ሌሊት ትመጣለችና”
ለአስገዳጅ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ከቤት አለመውጣት : አለመጨባበጥ : እጅን መታጠብ ወዘተ የመሳሰሉ ጥንቃቄዎችን እንድናደርግም መመሪያ ተሠጥቶናል:: ይህንን የቤተ ክርስቲያን መመሪያ ከእምነት መጉደል ቆጥሮ የሚተች ሰው ካለ በጠንካራ እምነቱ ኮሮናን በማስወገድ እንዲገላግለን በትሕትና እንማጸነዋለን::
“ከቤት አትውጡ” “ይህንን አታድርጉ” ማለት ከቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ ሳይሆን ከራሱ ከእግዚአብሔር አንደበት ተነግሮ ያውቃል:: እስራኤልን ከግብፅ ባርነት ነጻ ባወጣበት ምሽት በወረደው መቅሰፍት እስራኤል ከቤት ክትት እንዲሉ ተነግሮአቸው ቆይተዋል:: ምንም መቅሠፍቱ ለግብፃውያንን የወረደ ቢሆንም መልአከ ሞት ግን ከበር ውጪ ያገኘውን ማንኛውንም ፍጡር ይገድል ነበር እንጂ እስራኤል በፈጣሪ አምነናል ብለው ከቤት ውጪ እንዲንሸራሸሩ አልተፈቀደላቸውም::
ወደ ኁዋላ አትዙሩ ከተባለም አርፎ ወደፊት ማየት እንጂ እንደ ሎጥ ሚስት ቃኘት ቃኘት ማድረግ የጨውና ድንጋይ ዓምድ ያደርጋል:: እንደ ሎጥ ሚስት ወደ ኁዋላ አትዙሩ የተባለው ለአዲስ አበባ ሕዝብ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ በአንድ ሳምንት ብቻ በጨው ምርት ከዓለም አንደኛ ትሆን ነበር::
“ውይ ሳምኩሽ ጉንፋን እንዳላስይዝሽ” የሚለው የዋህ ሰላምተኛ ወገኔ መጠንቀቅ በሚቻለው ካልተጠነቀቀ የሚጠብቀን ከባድ ፈተና ነው:: ኃጢአታችንን በንስሓ እናጥባለን ወረርሽኝን ግን በቀላሉ ማጠብ አይቻልም::
እርግጥ ነው እምነት ያድናል:: ሆኖም ያመኑት ሁሉ ከበሽታ ይድናሉ የሚል መጽሐፍ የለም:: ሁሉም ሰውም እኩል የእምነት ደረጃ የለውም:: ዳስሶኝ እድናለሁ የሚል አለ : ጨርቁን ብነካ እድናለሁ የሚል አለ : ቃል ብቻ ተናገር የሚል አለ:: አምነው ዳኑ እንደሚል አምነው በክብር ሞቱም ይላል:: ቤተ ክርስቲያን የሁሉን ድካም አገናዝባ የእምነት ደረጃዎችን ሁሉ አቅፋ ትኖራለች:: እንደ ያዕቆባዊ ብልሃት በፈረስና በወጣት ጉልበት ሳይሆን በእምነት ሕፃናት በሆኑት እርምጃ ልክ ትራመዳለች:: (ዘፍ 33:14)
እውነተኛ እምነት ደግሞ መሞትንም የሚቀበል ነው:: ባንድንም እናምናለን ማለት ነው የሠለስቱ ደቂቅ እምነት:: እግዚአብሔርም ያመኑበትን ብቻ ለይቶ የሚጠብቅ የማያምኑበትን የሚተው አምላክ አይደለም:: “እርሱ ለሁሉ ፀሐይን ያወጣል ዝናምን ያዘንባል” ይላል ወንጌሉ:: እንደ ወንጌሉ እውነታ ከሆነ እንደውም ያመኑት ሞተው ያላመኑት ለማመን ጊዜ ቢሠጣቸው ይሻላል:: በእግዚአብሔር አምናለሁ ለሚል ሰው እንዲያውም ሊሔድና ከክርስቶስ ጋር ሊኖር የሚናፍቅ ነው:: ስለዚህ አምነን ለመሞት የጸና እምነት ከሌለን አምነን ለመዳንም የሚያበቃ እምነት የለንም ማለት ነው:: ወዳጄ አንተ በእምነትህ ትድናለህ የምትጨብጠው ሰውዬስ እምነት ካነሰው ለምን ይሙት?
አባቶች ተጠንቀቁ ብለው መግለጫ ሲሠጡ “አዬ አባት ጠፋ!” ብሎ የሚመጻደቅ ሰው ከቅርብ ቤተሰቡ አንድ ሁለት ሰው ድንገት ቢሞትበት “ለምን ታስፈጁናላችሁ ጸሎቱስ ቢቀር ምናለ? ብዙ ዓመት ተጸልዮ የለም እንዴ?” እንደሚል ጥርጥር የለውም:: ስለዚህ መጠንቀቅ በምንችለው አለመጠንቀቅ በቸልታ ራስን መግደል እንዳይሆን ያሳስባል::
ኮሮና ቫይረስ የሚገድለው አረጋውያንን ነው ብለው የሚጽናኑ እና የሚዘናጉ ብዙ ሰዎች አሉ:: ወዳጄ እሱ ዜና የሚሠራው ብዙ ሆስፒታል ባለበትና በቂ የመተንፈሻ መሣሪያዎች ባሉበት የአውሮፓ ሕክምና ነው:: የጉዋንት እጥረት ባለባት ሀገር ግን በሽታው እድሜ እያገናዘበ ሊገድል አይችልም::
ከቤት አትውጡ የሚባለው ቢያንስ የበሽታውን ሥርጭት ለማዘግየት ነው:: በአንዴ ከተሠራጨ ሁሉም ሰው በአንድ ቀን ወደ ሆስፒታል ይጎርፋል:: የባለሙያም የህክምና መስጫ መሣሪያም እጥረት ይከሰታል:: (መሣሪያውም ካለ ነው) ሐኪሞችም በጫና መብዛት ይዳከማሉ በሽታ የመከላከል አቅማቸውም ይቀንሳል:: ለወገን ሊቆሙ ታጥቀው የቆሙት ባለ ብዙ ብሶት ሐኪሞቻችንን አርፎ በመቀመጥ እንኩዋን ትብብር ብናደርግላቸው ይህን ያህል ትልቅ ነገር ነው?
አንተን አይገድልህ ይሆናል : የአንተ ንዝህላልነት ግን ሀገሪቱን ሽማግሌ አልባ ያደርጋታል:: ወጣትንም አይተውም:: ለወላጆቻችን ስንልም መጠንቀቅ እየቻልን “አባዬ እማዬ” ብንል ዋጋ የለውም:: ለመቀባበርም ጤና ያስፈልጋል:: መንግሥትም የየትኛውም ፓርቲ ደጋፊ ያልሆነ በሽታ መምጣቱን ተረድቶ አላስፈላጊ ስብሰባዎችን ማስቆም : ከምግብና ጤና ነክ ውጪ ያሉ የሥራ እንቅስቃሴዎችን ማስቆም ይገባዋል:: ሁኔታዎች ሳያስቆሙን እኛ ማቆም የምንችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ:: ለጥቂት ጊዜ መሸሸግ እጅግ መልካም ነው::
+ የኮሮና ሌላው ገጽታ +
በዚህ ወቅት በቤት ለመቆየት ለተገደዳችሁ ሁሉ! ነገም ለምትገደዱ ሁሉ! ሓላፊነት ተሰምቶአችሁ ከእንቅስቃሴ ለተገታችሁ ሁሉ በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት እነዚህን መልካም ዕድሎች አታሳልፉ እነዚህንም አስታውሱ
1. ንስሓ ዋነኛው ነው
ወደ እግዚአብሔር በንስሓ መቅረብ ከተጣሉት መታረቅ : የበደሉትን ይቅርታ መጠየቅ : የተቀየሙትን ይቅር ማለት ጊዜው አሁን ነው:: የማናናግራቸው የዘጋናቸውን ሰዎች እስቲ ዛሬ እናስባቸው:: በሞት ጥላ ተከብቦ የማይታረቅ የለምና ይህንን ጊዜ ለሰላም እናድርገው:: በንግግር ያቆሰልናቸውን በፍቅር ቃል እንካሳቸው:: ምሕረት የሚወርደውም በዚህ ነው::
2. መከራ የጸሎት ትምህርት ቤት ነው
በጨነቀኝ ጊዜ ሁሉ እግዚአብሔርን ጠራሁት ይላል ነቢዩ:: በደስታችን ጊዜ የምንረሳው ፈጣሪም “በመከራህ ቀን ጥራኝ እኔም እሰማሃለሁ” ይላል:: እርግጥ ነው ብዙዎቻችን ስለ ፈጣሪ የምናስበው በጭንቅ ቀን ነው:: እርሱ ግን የት ከርመህ ሲጨንቅህ አስታወስከኝ አይልም:: “እግዚአብሔር መልካም ነው በመከራ ቀንም መሸሸጊያ ነው”
ይህ ወቅት ጸሎት የምንማርበት ወቅት ነው:: በተለይ ውስጥን ጸጥ የሚያደርገውን መዝሙረ ዳዊት ለመጸለይ ጊዜው አሁን ነው:: ጊዜ የለኝም ብለን ያላነበብናቸውን መጻሕፍት ያልተማርናቸውን ትምህርቶች ያልሰራናቸውን የቤት ሥራዎች የምንሠራበት ወቅት ነው:
3 ከቤተሰብ ጋር ጊዜ ማሳለፊያ ወቅትም ነው
በሥራ በትምህርት በማኅበራዊ ሩጫ ምክንያት ቤተሰቦቻችንን የዘነጋን ብዙ ነን:: ልጆቻቸው የሚደውሉበትን ቀን በናፍቆት እየጠበቁ ስልካቸውን በጉጉት የሚያዩ : ከሰላምታ ባለፈ ቁጭ ብለን የማናናግራቸው : የሚሰማቸው ያጡ አያቶቻችን እናት አባቶቻችንን ቁጭ ብለን የምንሰማበትና የማይረሳ ጊዜ የምናሳልፍበት ጊዜ ይኼ ነው::
4. ይህ ጊዜ የምጽዋት ጊዜ ነው
በእንቅስቃሴ መገታት ምክንያት ብዙ ሥራዎች ይቆማሉ:: በሀብታሞቹ ሀገራት እንኩዋን ወደ ነበርንበት የዕለት ተዕለት ኑሮ ለመመለስ ቢያንስ አራት ወራት ያስፈልጋል እያሉ ነው::
ወዳጄ ዛሬ በእኛ ሀገር “ከቤት አትውጡ” ሲባል ቤት የሌላቸውም እንዳሉ አንዘንጋ:: ረሃብ ሳይመጣ ሸምቱ ሲባል ለዕለት ጉርስ ያጡ እና ራቴን ፈጣሪ ያውቃል የሚሉ ብዙዎች ናቸው:: እኛ ስለ ጉዋንትና አፍ መሸፈኛ በፋርማሲ ደጅ ተሰልፈን ስንጨቃጨቅ ምን እየተከናወነ እንደሆነ ግራ የሚገባቸው ዕርቃናቸውን መሸፈኛ ያጡ ብዙ ናቸው:: “በሳጥንህ ውስጥ ያስቀመጥካቸው የማትለብሳቸው ልብሶች የወንድምህ ልብሶች ናቸው” ይላል ቅዱስ አምብሮስ:: በዚህ ሰዓት ከመስገብገብ ለወገን ማሰብ የተሻለ ነው:: ከክፉ የሚድነውም የራሱን ደህንነት ብቻ የሚያስብ ሳይሆን እንደ ሰራፕታዋ መበለት”በማድጋ ካለው ከእፍኝ ዱቄት፥ በማሰሮም ካለው ከጥቂት ዘይት በቀር እንጀራ የለኝም፤ እነሆም፥ ገብቼ ለእኔና ለልጄ እጋግረው ዘንድ በልተነውም እንሞት ዘንድ ጥቂት እንጨት እሰበስባለሁ” ማለትና ለኤልያሶች እንጎቻ መጋገር የቻለ ነው:: ሁኔታዎች እስኪስተካከሉ ቢያንስ ወራት ይወስዳል:: በረሃብ ጊዜ ደግሞ መተዛዘን የግድ ያስፈልጋል::
“አቤቱ፥ በቍጣህ አትቅሠፈኝ፥ በመዓትህም አትገሥጸኝ” መዝ ፮፥ ፩