የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን St. Gabriel Church

የኮሮና ቫይረስ መረጃዎች ማቅረቢያ ገጽ Coronavirus update page

የታኅሣሥ ቅዱስ ገብርኤል በዓለ ንግሥ በቀጥታ

  • ቀጥታ ይከታተሉ Go Live
  • CDC BC
  • PHA Canada
  • Ethiopian PHI
  • Eritrean MOH
  • WHO
  • CDC U.S.
  • ስዕላዊና ቁጥራዊ መረጃዎች >>>
  • Rank (Live update)
  • Canada’s Dashboard
  • WHO’s Dashboard
  • Ethiopia’s Dashboard

የኮሮና ቫይረስን (COVID-19) አስመልክቶ ከሰበካ ጉባኤ የተሰጠ ማሳሰቢያ ሰኔ ፲፮

June 24, 2020 by admin Leave a Comment

የኮሮና ቫይረስን (COVID-19) አስመልክቶ ከሰበካ ጉባኤ የተሰጠ ማሳሰቢያ

“ነገር ግን ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን”

፩ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች ፲፬፥ ፵

Read in English here

ከሁሉም አስቀድመን በየዘመናችን ሁሉ ለጠበቀንና በነገር ሁሉ ለረዳን የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ምስጋናችንን እናቀርባለን። የመልአኩ ቅዱስ ገብርኤልና ይልቁንም የሰማዕቱ ቅዱስ ቂርቆስ ቃልኪዳንና ጸሎት ተራድቶን የአጥቢያችን የአምልኮ ሥርዓት ሳይታጎልና የምዕመናንም አንድነት እየጠነከረ ለዚህ ጊዜ ደርሰናል። አሁን ላይ በመንግስት የመልሶ አገልጎት መጀመር እቅድ (restart Plan) ምክንያት ምዕመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን እየመጡ ለምስጋናና ለአምልኮ መሰጠታቸውን እናደንቃለን። በዚሁ አጋጣሚ በተለያዩ ጊዜያት ምዕመናን ለሚሰጡት አስተያየትና ድጋፍ አክብሮታችንን እየገለጽን በቀጣይም በአገልግሎታችን ውስጥ የበለጠ ጥንቃቄ ለማደርግና የጠላት ዲያቢሎስን ፈተኛዎች ለመታገል እንዲረዳን እንዲሁም የግዛቱ ጤና መኮንን የሚሰጡትን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ እንዲያስችለን የሚከተሉትን ማሳሰቢያዎች ለማስተላለፍ እንፈልጋለን።

  1. አሁንም ቢሆን የሁለት ሜትር አካላዊ ርቀት እንደተጠበቀ እንዲቀጥል
  2. በአምልኮ ሥርዓት የሚገኙ ምዕመናን ቁጥር ከሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ስፋት አንጻር ገደብ ስለሚጥለብን እስከ ፲፭ ሰዎች ብቻ በየአገልግሎቱ እንዲገኙ
  3. በሰንበተ ክርስቲያን እሑድ ቅዳሴ የምትገኙ ምዕመናን ከሑሙስ አስቀድማችሁ ከዚህ በታች ለተጠቀሱት አንዳቸው እንድታሳውቁ
  4. አርአያ ገ/ማርያም በስልክ 250-217-6365 ወይም
  5. ኤርምያስ ኃይሌ በስልክ 778-966-1414
  6. ሳታስታውቁ የቀራችሁ በዙም በሚተላለፈው መርሃግብር እቤታችሁ አምልኮታችሁን እንድትፈጽሙ። ከላይ የተጠቀሱት አባላትም የምዕመኑን ቁጥር ገደብና አካላዊ ርቀት ቁጥጥር እንዲያደርጉ ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት የመደባቸው መሆኑን እናሳውቃለን።

ይህንን ጊዜ በደህና አሳልፎልን በምልአት ከቅጽረ ቤተ ክርስቲያን አምልኳችንን ለማከናወን እንዲያደርሰን ፈጣሪያችንን እየተማጸንን ለአባታዊ ክትትል፣ ምክርና የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት

  • ቀሲስ አበበን  በስልክ 778-677-9607 በኢሜይል: chair@stgabrieleotcvictoria.org

 ለማኅበራዊ መስተጋብር፣ መረጃዎችና እገዛዎች የክፍሉን ኃላፊ

  • ዶ/ር ዮናስን  በስልክ 250-813-2056 በኢሜይል: saar@stgabrieleotcvictoria.org      እንድታገኟቸው ይሁን።

ልዑል እግዚአብሔር ማኅበራችንን ያስፋልን ይጠብቅልን አሜን

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ ጽ/ቤት

Posted in: መረጃ, ኮሮና ቫይረስ Tagged: A solution to Coronavirus, BC, Canada, Coronavirus, COVID-19, EOTC, Ethiopia, God is the solution, Parish, Prayer is powerful, Victoria, ሰበካ ጉባኤ, ኮሮናቫይረስ

የኮሮና ቫይረስን (COVID-19) አስመልክቶ ከሰበካ ጉባኤ የተሰጠ ማሳሰቢያ ፪

March 28, 2020 by admin Leave a Comment

ሕዝቤ ሆይ፥ ና ወደ ቤትህም ግባ፥ ደጅህን በኋላህ ዝጋ፤ ቍጣ እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ

ኢሳ ፳፮፥፳

በመላው ዓለም ላሉ የሰው ልጆች ከፍተኛ ሥጋት በመሆን በፍጥነት እየተስፋፋና እየተዛመተ የሚገኘው የኮሮና ቫይርስ በተመለከተ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምዕመኗን ለመታደግ ሃይማኖታዊ መመሪያ እየሰጠች ትገኛለች። የደብራችን ሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤም የሁኔታውን አሳሳቢነት በማየትና በምዕመናን ላይ ያለውን ማኅበራዊ ተግዳሮት በመረዳት መሠረተ እምነትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በጠበቀ መልኩ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አስተላልፏል።

  1. ከዚህ ቀደም የተላላፉት ውሳኔውች እንደተጠበቁ እንዲቀጥሉ
  2. በሳምንት ሁለት ቀን የምህላ ጸሎትና የሰንበት ቅዳሴ አገልግሎት የሚኖር ሲሆን አገልግሎቱ ባሉን ካህናት ብቻ እንዲከናወን፤ የምህላውን ቀን በየሳምንቱ ለምዕመናን እንዲገለጽ
  3. ምዕመናን ከቤታችሁ በመሆን በጾምና ጸሎት፣ በልቅሶ ወደ ፈጣሪ እንድታሳስቡ
  4. ቤተ ክርስቲያን እዚህ ያለውን አገልግሎት ተደራሽ እስከምታደርግ ከቫንኮቨር ኆኅተ ሰማይ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን የሚተላለፉ የቀጥታ አገልግሎቶችን ቫይበር ላይ በተላለፈው መመሪያ መሠረት መተግበሪያውን በመጠቀም እንድትከታተሉ፤ ለዚህም ጌዜና ቦታ በመወሰን ከነቤተሰቦቻችሁ ተካፋይ እንድትሆኑ
  5. ምዕመናን ከቤተ ክርስቲያኗ የምትፈልጉት አገልግሎት ሲኖር ቀሲስ አበበን በመጠየቅ እንድትመካከሩ
  6. ከማኅበረ ምዕመናን በሕመም፣ በሥራ ማጣትና ሌሎች የግልና ማኅበራዊ ጉዳዮች ለሚገጥሟችሁ ተግዳሮቶች መረጃዎችን ወደ ዶ/ር ዮናስ እንድታደርሱ፤ ማኅበራዊ ክፍልና ሰበካ ጉባኤውም ከምዕመናን የሚመጡ የእገዛ ጥያቄዎች ለማስተባበርና ምዕመናኑ እርስ በእርሱ እንዲተሳሰብና እንዲጠያየቅ እንዲያደርጉ ውሳኔ አስተላልፏል።

ወደፊትም ሁናታዎችን በየጊዜው እየተከታተልን አስፈላጊ እርምጃዎችንና ውሳኔዎችን የምናሳውቃችሁ ሲሆን እስከዛው ባላችሁበት የምታነቡትና መረጃዎችን የምትከታተሉበት ለዚህ ተብሎ የተዘጋጀውን ድረ ገጽ (https://stgabrieleotcvictoria.org/health) ላይ እንድትከታተሉ እናሳስባለን።

  • ቀሲስ አበበን ለማግኘት በስልክ 778-677-9607 በኢሜይል: chair@stgabrieleotcvictoria.org      
  • ዶ/ር ዮናስን ለማግኘት በስልክ 250-813-2056 በኢሜይል: saar@stgabrieleotcvictoria.org      

በአጠቃላይ በበሽታው እስካሁን ለተያዙትና በጊዜያዊ ማቆያ ለሚገኙት እግዚአብሔር አምላክ ምህረቱን እንዲሰጥልን እንለምናለን። በበሽታውም ወገኖቻቸውን ለተነጠቁት ሁሉ መጽናናትን እንዲሰጥልን ያረፉትምንም እንዲምርልን እንጸልያለን።

ልዑል እግዚአብሔር በይቅርታው ብዛት ሁላችንንም ከመከራ ሞት ይጠብቀን ዓለማችንንም ከጥፋት ይሰውርልን። አሜን

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ

Posted in: መረጃ, ኮሮና ቫይረስ Tagged: A solution to Coronavirus, BC, Canada, Coronavirus, COVID-19, EOTC, Ethiopia, God is the solution, Parish, Prayer is powerful, Victoria, ሰበካ ጉባኤ, ኮሮናቫይረስ

የቋሚ ሲኖዶስ መግለጫ ፫

March 27, 2020 by admin Leave a Comment

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ብዙዎችን መምሪያዎች በጊዜያዊነት መዝጋቱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዛሬው ዕለት ባካሔደው ስብሰባ ብዙዎችን መምሪያዎች ሙሉ በሙሉና ለአስቸኳይ ሥራ የሚፈለጉትን ደግሞ በከፊል በጊዜያዊነት መዝጋቱን አስታወቀ።
ሙሉ በሙሉ የተዘጉ መምሪያዎች የመንበረ ፓትርያርክ ቅርሳቅርስ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር፣ ጉብኝት፣ የንባብ አገልግሎት፣ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ኮሌጆች፣ ሥልጠና ያልጀመሩ የካህናት ማሠልጠኛዎች፣ መዋዕለ ሕፃናት፣ የአብነት ትምህርት ቤቶች ሲሆኑ በከፊል የተዘጉት ደግሞ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት እስከ አህጉረ ስብከት ለአስቸኳይ ሥራ የሚፈለጉት መሆናቸውን ገልጧል።

Posted in: መረጃ, ኮሮና ቫይረስ Tagged: Coronavirus, COVID-19, EOTC, Ethiopia, God is the solution, Holy Synod, how to treat COVID-19, Prayer, Prayer is powerful, Return to God, The Orthodox way, ቅዱስ ሲኖዶስ

ብንሞትም ብንኖርም ለእግዚአብሔር

March 23, 2020 by admin 1 Comment

ብንሞትም ብንኖርም ለእግዚአብሔር ነው

ሮሜ ፲፬፥ ፰ /14: 8/

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን፡፡

በዲያቆን ብርሀኑ አድማስ

ትላንት እህቴ ከጣልያን ሚላኖ ከነገረችኝ ውስጥ በጣልያን በኮረና ቫይረስ ምክንያት ከተፈጠረው ፍርሃትና ጭንቀት የተነሣ ስድስት ሰዎች በጭንቀት ራሳቸውን ከፎቅ ወርውረው ውድ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ይህ በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ ምክንያቱም በበሽታው ቢያዙ እንኳ ከሞት የከፋ የሚደርስባቸው አልነበረም፡፡ ሲሆን ደግሞ ላይያዙም ይችሉ ነበር፤ ወይም ታምመው ሊድኑ እየቻሉ እንዲሁ በጭንቀትና በፍርሃት ራስን በዚህ መንገድ እስከማጣት መድረስ አንዳንድ ጊዜ አስተያየት ለመስጠትም ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም ራሳቸውን ያጠፉት ሞትን ፈርተው ነውና፡፡ ስለዚህም ፍርሃታቸውና ጭንቀታቸው ሞታቸውን ከማስቸኮሉ በቀር አልጠቀማቸውም። ራሳቸውንም ለመቆጣጠርም አቅም አጥተው ቀድመው እስኪሞቱ ድረስ ራሳቸውን መሳታቸው በእጅጉ ያሳዝናል፤ ልብንም ይሰብራል፡፡

ወደ አውሮፓ ለመግባት በደካማ ጀልባዎች ሲጓዙ በባሕር ውስጥ የሚያልቁ አፍሪካውያንን ሬሳዎች ለቅመው ሰብስበው የሚቀብሩ ብዙ ደግ ሰዎች ያሉባት ጣልያን እንደዚህ በሆነ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ከበሽታው ጋራ ተስፋ መቁረጥም ሲቀጣቸው ማየት በእውነት በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ ከዚህም ሁሉ ጋር ደግሞ በየቤታቸው ያሉት የሰዎችን ጭንቀት እንደመስማት ያለ የሚያሳዝን ነገር የለም፡፡ ትላንት በስልክ ካነጋገረችኝ እህቴ ጋር የነበረችኝን አጭር የስልክ ቆይታ ለመጨረስ ምን ያህል አስጨናቂ እንደነበርና ስሜትን ተቆጣጥሮ ለመነጋገር ምን ያህል እንደተቸገርኩ ሳሰብ የተፈጠረው ጭነቀትና ፍርሃት አሁንም በእጅጉ ያሳስበኛል፡፡

ከዚህም ሁሉ ጋር ብዙ ክርስቲያኖች ካህን ለማናገር ፈልገው አለመቻላቸው፣ ጸበል ፈልገው አለማግኘታቸው፣ መቁረብ ፈልገው አብያተ ክርስቲያን ዝግ መሆናቸውና መንቀሳቀስ የማይፈቀድላቸው መሆኑ ተጨማሪ ፍርሃትና ሐዘን እንደጨመረባቸው መስማትም ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡

ታዲያ ምን እናድርግ

በተለይ በውጭ ሀገር ላላችሁና ይህን መልእክት ማንበብ ለምትችሉ ሁሉ መፍትሔ የምላቸውን እንደሚከተለው እጠቁማለሁ፡፡

1) ሚዲያው በሚፈጥረው ጫና ምክንያት የሚፈጠርባችሁን ጭንቀት ለመቀነስ ስለበሽታው ዕድገት ሥርጭትና አሳሳቢነት ብቻ የሚተላለፉ ዜናዎችን፣ ሐተታዎችን በቀን ከአንድ ጊዜ በላይ መስማት ብታቆሙ መልካም ይመስለኛል፡፡ እንዲያውም ከተቻለ በጉዳዩ ላይ በተለያዩ ሚዲያዎች ከሚቀርቡት ትንታኔዎች መካከል በተለየ መንገድ የሚቀርቡና በሽታውን በሌላም መንገድ ማለትም በእውነተኛ የሰው ልጆች ሕይወት ገጠመኝ ውስጥ እንዳንዱ ብናየው መልካም ሊሆን ይችላል፡፡

2) ንስሐ ለመፈጸም፣ ጸበል ለመጠጣት ለመቀባባት፣ ለመጠመቅ፣ ቁርባን ለመቁረብ ፈልጋችሁ በችግሩ ምክንያት ያላገኛችሁ ከማድረግ ልታገኙ የምትችሉትን ሥርየትም ሆነ በረከት እንዳጣችሁ ማሰብ የለባችሁም፡፡ የመጀመሪያው የሚያስፈልገው ተስፋ በመቁረጥና በመጨነቅ ሳይሆን በተሰበረ ልቡና ሆኖ የንስሐ ዕንባ ከዐይናችን የምናፈስስ ከሆነ ሁሉም ከላይ የፈለግናቸው ነገሮች በእምነት ይደረጉልናል፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ በቅዳሴው እኛ ስላሉን ሦስት ልደቶች ሲያብራራ ፡- አንዲቱ ክርስቶስን የምታስመሰለን ቅድስት ጥምቀት ናት፡፡ አንዱም በደልንና ኃጢአትን የሚያስተሠርይ የክርስቶስ ሥጋውና ደሙ ነው፡፡ አንዱም ንጹሕ አድርጎ ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርብ ከሰውነት ውስጥ በዮርዳኖስ አምሳል የሚወጣ በንስሐ ያለ እንባ ነው፤ እንዳለ በአሁኑ ጊዜ የሚደረግ እውነተኛ የንስሐ እንባ በዮርዳኖስ ተጠምቆ በኃጢአት ያጎሰቆልነውን ልጅነት የሚያድስልን ስለሆነ እውነተኛ ጸበል ነውና ጸበል አላገኘንም አትበሉ፡፡

እውነቱን ለመናገር በፍጹምነትና በእምነት የምናመልከው ከሆነ በመቅድም ተአምረ ማርያም ላይ እንደተጻፈው የተቻለው ሥጋውን ደሙን እየተቀበለ ያልተቻለው ደግሞ የእመቤታችን ተአምራት በተለያየ መንገድ እየሰማ ይደረግልኛል እያለ ቢያምን ልክ እንደተቀበለ ይሆንለታል፤ ይደረግለታልና ሳይቻለን ባላገኘነው ነገር አንጨነቅ አንፍራ፡፡ ይልቁንም እንመን፣ እንጽና፡፡ አስተውሉ ክርስቲያኖች፤ እመቤታችን ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም የሰው ዘር (የባሕርያችን) እውነተኛና ብቸኛ መመኪያ ናት፡፡ በመጽሐፍ እንደተጻፈ ከእርሷ በቀር አካላዊ ቃልን ለመቀበል የተገባው አልተገኘም። እርሷ ግን የተገባት ሆና ተገኝታለችና በእርሷ አማላጅነት ልባችንን እናሳርፍ፡፡ ስለዚህ በአማልጅነቷ አምነን ከልጇ ታስታርቀን ዘንድ ተስፋና እምነት ባልተለየው የንስሐ እንባ እንለምናት፤ ልታማልደን የታመነች የምሕረት እመቤት ናትና፡፡ ተአምሯንም እንስማ፡፡ ከዚህም ሁሉ ጋር በቤታችን ሆነን በጸጥታ በሚዲያና በወሬ ሳናቋርጥ ወንጌልን እናንብብ፣ በጸሎትም ዘግተን እንነጋገር፤ ይህን ብናደርግ መድኃኒትና መፍትሔ ስለሚሆነን እንረጋጋለን፤ ክፉውንም እናሸንፋለን፡፡ እምነትና ተስፋ ተለይቶን ከሆነ ግን ዕድሉን አግኝተን ጸበል ብንጠጣና ብንቆርብም ትርጉም አይኖረውም፡፡ ስለዚህ አምነን ባለንበት በቤታችን ሆነን በእምነት ጸንተን፣ በተስፋ ተሞልተን ቅዱሳት መጻሕፍትን እየሰማን እንጸልይ ዘንድ እማጸናችኋለሁ፡፡

3) ለዚህ ጽሑፍ በመጨረሻ ማንሣት የምፈልገው አሁንም በእግዚአብሔርና እርሱ ባከበራቸው በቅዱሳኑ ላይ ያለንን መተማመን እንድናሳድግ ነው፡፡ በጣም የሚገርመኝ ሚዲያውን የምናምነውን ያህል በቅዱሳን ገድል ብናምን ምን ያህል በተጠቀምን ነበር፡፡ ሰዎች አፋቸውን ሞልተው በሳይንስ አምናለሁ ይላሉ፤ እኛስ አፋችንን ሞልተን በፈጣሪና በሥራው ለምን አናምንም?

ለምሳሌ ስለበሽታው በሳይንስ የሚመከረውን እንደምንቀበለው ሁሉ በእምነት ያለውንም መቀበል አስፈላጊ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር የሴራ ተንታኞች ቫይረሱ አውቀው የፈጠሩት ነው፤ እገሌን ለማጥቃት ነው፣… የሚለውን ወሬ ከማዳነቅ ያ ሆነም አልሆነም እንዲህ ያለው ትልቅ ክስተት ያለፈጣሪ ፈቃድም እኮ አይከሰትም፡፡ ኢዮብ ላይ ብቻ ያን ሁሉ መከራ እንዲያመጣ ፈጣሪ ለሰይጣን እንደፈቀደለት ልክ እንዲሁ ለመቅሰፍትም ለተግሣጽም ወይም ለማናውቀውም ምክንያት ፈጣሪ ክፉው ሰይጣን በእኛ ላይ ሊያደርግ የሚፈቅድለት ጊዜ እንዳለ ከታሪክም ከቅዱሳት መጻሕፍትም ተምረናል፡፡

እኔ በግሌ እንዲህ ያለው ተላላፊ በሽታ ያለ ሰይጣን የሚደረግ ነው ብዬ ለመቀበል አልችልም፡፡ ይህም ማለት ሰይጣን በብዙ መንገድ በሽታዎችን ያመጣል፤ የተፈቀደለት ጊዜም አጭር ስለሚሆን እንዲሁ በፍጥነት አዳርሶ ብዙዉን ረብሾ ተስፋ አስቆርጦ ከቻለም አስክዶ ሥጋንም ነፍስንም መንፈስንም አጎስቁሎ ለመሄድ ይፋጠናል፡፡ በድርሳነ ሚካኤል ላይ እንደተገለጸው አብዛኛዎቹ እንዲህ ያሉ በሽታዎች ከመናፍስት ጋር የተያያዙ ስለሆነ እንደ ድርሳነ ሚካኤል፣ ድርሳነ ገብርኤል፣ ድርሳነ ሩፋኤል፣ ገድለ ቂርቆስ፣ ገድለ አቡነ ሀብተ ማርያምና በመጨረሻም ሁልጊዜም ቅዱስ ወንጌልን በመስማትና በመጸለይ ብናጠቃልለው ልንቋቋመውና ልናሸንፈው እንችላለን፡፡

በትዝታ ዘአለቃ ለማ ላይ እንደተገለጸው ልቡሰ ሥጋ የሚባለው በሰው ላይ ደዌ በማምጣት የሚታወቀው መንፈስ በሚያደርስባቸው ጥቃት አባቶቻችን በጭንቅ ከታመሙ በኋላ ሁሉ እንኳ እንዴት በጸሎትና በእምነት ድል እንደሚነሡት ብዙ ጊዜ የሰማን ያነበብን ይመስለኛል፡፡ ያን የሰማነውን ያነበብነውን ሁሉ አስታውሰን በእንዲህ ያለው ወቅት ካልተጠቀምንበትና ከጭንቀት፣ ከፍራሃትና ከእምነት ማጣት በመጨረሻም ከተስፋ መቁረጥ ካልተጠበቅንበት ለመቼ ያገለግለናል? ወይስ መጻሕፍቶቻችን ሀሉ ልቦለድ ይመስሉናል? እንግዲያውስ እምነታችን አጽንተን በፍጹም ተስፋ ተሞልተን እንጸልይ እንጂ አንጨነቅ፡፡

ቤት መዋላችንም ቢሆን በቤት መዋል ካለማወቃችንና በወከባ ውስጥ ከመኖራችን የተነሣ ጭምር ከብዶን ይሆናል እንጂ ምን አልባት እግዚአብሔር ለሕይወታችን መረጋጋትም እያስተማረን ስለሚሆን እንደ እሥራት አንቁጠረው፡፡

ሁሉንም ለእግዚአብሔር ክብር የምንችለውን ሁሉ ካደረግን በኋላ ግን ብንኖርም ለእግዚአብሔር ለመኖር (በንስሐችን ጸንተን) ብንሞትም ለአግዚአብሔር (ከእርሱ ጋር ለመኖር) መሆኑን አምነት እርስ በእርሳችን መጽናናትና መረጋጋት ይገባናል፡፡ የሰንበት ጌታ፣ ለሰው ድኅነት ሲል ሰንበትን ሳይቀር ሽሮ ሰውን የፈወሰ ይቅር ያለና ሰንበትም ለሰው እንጂ ሰው ለሰንበት ያልተፈጠረ መሆኑን ያስተማረ አምላክ አሁንም በሆነው ብዙዎችን ወደ እርሱ ያቀርበን ዘነድ በበሽታውም የታመሙትን ሁሉ ይፈውስ ዘንድ፣ በሽታ በሚያመጣው ክፉ መንፈስ የተጠቃነውን ብቻ ሳይሆን፣ በስስት፣ በስግብግብነት፣ በምቀኝነትና በቅንዓት፣ በምቾትና በቅምጥልነት እንዲሁም በሌሎች ክፉዎች መናፍስት ተወግተን ወድቀን ከእግዘኢብሔር የተለየነውን ሁሉ ይቅር ብሎ ዛሬም በከበረ ደሙ ፈሳሽነት ዐለምን ይቅር ይለው ዘንድ የእርሱ ፈቃድ ይሁንልን፡፡ የእናታችን የእመቤታችን የንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃ፣ የቅዱሳን መላእክት ጥበቃ፣ ከሴቶች ከተወለዱት የሚተካከለው የሌለው የመናኙ ነቢይ ሐዋርያና ሰማዕት የሆነው የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ እና የሌሎች ቅዱሳን ሁሉ ምልጃና ጸሎት ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን፡፡

Posted in: መረጃ, ኮሮና ቫይረስ Tagged: A solution to Coronavirus, BC, Canada, Coronavirus, COVID-19, EOTC, Ethiopia, God is the solution, Holy Synod, how to treat COVID-19, Parish, Prayer is powerful, Return to God, Save me, The Orthodox way, Victoria, ምን እናድርግ

በኮሮና ዋዜማ

March 23, 2020 by admin Leave a Comment

 በዲያቆን ሔኖክ ኃይሌ

ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በይፋ ጉባኤያትን አቁማለች:: የነፍስ ሕይወት መድኃኒት የሆነ ሥጋ ወደሙን ለመቀበል በምንገኝበት ቅዳሴና በጸሎተ ዕጣን ጊዜ ደግሞ ከማኅበራዊ ፈቀቅታ ጋር በጥንቃቄ እንድናደርግ እና ከአባቶች ጋር በቅርበት የሚሠሩ የጤና ባለሙያዎችን ምክር እንድንሰማ አሳስባለች:: ይህንን የጥቂት ጊዜ ዕድልም ብንሞትም ብንኖርም ለክርስቶስ የሚያደርገንን ጸጋ ለማግኘት ለንስሓና ለቁርባን እንጠቀምበት:: “ማንም ሊሠራባት ከማይችልባት ሌሊት ትመጣለችና”

ለአስገዳጅ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ከቤት አለመውጣት : አለመጨባበጥ : እጅን መታጠብ ወዘተ የመሳሰሉ ጥንቃቄዎችን እንድናደርግም መመሪያ ተሠጥቶናል:: ይህንን የቤተ ክርስቲያን መመሪያ ከእምነት መጉደል ቆጥሮ የሚተች ሰው ካለ በጠንካራ እምነቱ ኮሮናን በማስወገድ እንዲገላግለን በትሕትና እንማጸነዋለን::

“ከቤት አትውጡ” “ይህንን አታድርጉ” ማለት ከቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ ሳይሆን ከራሱ ከእግዚአብሔር አንደበት ተነግሮ ያውቃል:: እስራኤልን ከግብፅ ባርነት ነጻ ባወጣበት ምሽት በወረደው መቅሰፍት እስራኤል ከቤት ክትት እንዲሉ ተነግሮአቸው ቆይተዋል:: ምንም መቅሠፍቱ ለግብፃውያንን የወረደ ቢሆንም መልአከ ሞት ግን ከበር ውጪ ያገኘውን ማንኛውንም ፍጡር ይገድል ነበር እንጂ እስራኤል በፈጣሪ አምነናል ብለው ከቤት ውጪ እንዲንሸራሸሩ አልተፈቀደላቸውም::

ወደ ኁዋላ አትዙሩ ከተባለም አርፎ ወደፊት ማየት እንጂ እንደ ሎጥ ሚስት ቃኘት ቃኘት ማድረግ የጨውና ድንጋይ ዓምድ ያደርጋል:: እንደ ሎጥ ሚስት ወደ ኁዋላ አትዙሩ የተባለው ለአዲስ አበባ ሕዝብ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ በአንድ ሳምንት ብቻ በጨው ምርት ከዓለም አንደኛ ትሆን ነበር::

“ውይ ሳምኩሽ ጉንፋን እንዳላስይዝሽ” የሚለው የዋህ ሰላምተኛ ወገኔ መጠንቀቅ በሚቻለው ካልተጠነቀቀ የሚጠብቀን ከባድ ፈተና ነው:: ኃጢአታችንን በንስሓ እናጥባለን ወረርሽኝን ግን በቀላሉ ማጠብ አይቻልም::

እርግጥ ነው እምነት ያድናል:: ሆኖም ያመኑት ሁሉ ከበሽታ ይድናሉ የሚል መጽሐፍ የለም:: ሁሉም ሰውም እኩል የእምነት ደረጃ የለውም:: ዳስሶኝ እድናለሁ የሚል አለ : ጨርቁን ብነካ እድናለሁ የሚል አለ : ቃል ብቻ ተናገር የሚል አለ:: አምነው ዳኑ እንደሚል አምነው በክብር ሞቱም ይላል:: ቤተ ክርስቲያን የሁሉን ድካም አገናዝባ የእምነት ደረጃዎችን ሁሉ አቅፋ ትኖራለች:: እንደ ያዕቆባዊ ብልሃት በፈረስና በወጣት ጉልበት ሳይሆን በእምነት ሕፃናት በሆኑት እርምጃ ልክ ትራመዳለች:: (ዘፍ 33:14)

እውነተኛ እምነት ደግሞ መሞትንም የሚቀበል ነው:: ባንድንም እናምናለን ማለት ነው የሠለስቱ ደቂቅ እምነት:: እግዚአብሔርም ያመኑበትን ብቻ ለይቶ የሚጠብቅ የማያምኑበትን የሚተው አምላክ አይደለም:: “እርሱ ለሁሉ ፀሐይን ያወጣል ዝናምን ያዘንባል” ይላል ወንጌሉ:: እንደ ወንጌሉ እውነታ ከሆነ እንደውም ያመኑት ሞተው ያላመኑት ለማመን ጊዜ ቢሠጣቸው ይሻላል:: በእግዚአብሔር አምናለሁ ለሚል ሰው እንዲያውም ሊሔድና ከክርስቶስ ጋር ሊኖር የሚናፍቅ ነው:: ስለዚህ አምነን ለመሞት የጸና እምነት ከሌለን አምነን ለመዳንም የሚያበቃ እምነት የለንም ማለት ነው:: ወዳጄ አንተ በእምነትህ ትድናለህ የምትጨብጠው ሰውዬስ እምነት ካነሰው ለምን ይሙት?

አባቶች ተጠንቀቁ ብለው መግለጫ ሲሠጡ “አዬ አባት ጠፋ!” ብሎ የሚመጻደቅ ሰው ከቅርብ ቤተሰቡ አንድ ሁለት ሰው ድንገት ቢሞትበት “ለምን ታስፈጁናላችሁ ጸሎቱስ ቢቀር ምናለ? ብዙ ዓመት ተጸልዮ የለም እንዴ?” እንደሚል ጥርጥር የለውም:: ስለዚህ መጠንቀቅ በምንችለው አለመጠንቀቅ በቸልታ ራስን መግደል እንዳይሆን ያሳስባል::

ኮሮና ቫይረስ የሚገድለው አረጋውያንን ነው ብለው የሚጽናኑ እና የሚዘናጉ ብዙ ሰዎች አሉ:: ወዳጄ እሱ ዜና የሚሠራው ብዙ ሆስፒታል ባለበትና በቂ የመተንፈሻ መሣሪያዎች ባሉበት የአውሮፓ ሕክምና ነው:: የጉዋንት እጥረት ባለባት ሀገር ግን በሽታው እድሜ እያገናዘበ ሊገድል አይችልም::

ከቤት አትውጡ የሚባለው ቢያንስ የበሽታውን ሥርጭት ለማዘግየት ነው:: በአንዴ ከተሠራጨ ሁሉም ሰው በአንድ ቀን ወደ ሆስፒታል ይጎርፋል:: የባለሙያም የህክምና መስጫ መሣሪያም እጥረት ይከሰታል:: (መሣሪያውም ካለ ነው) ሐኪሞችም በጫና መብዛት ይዳከማሉ በሽታ የመከላከል አቅማቸውም ይቀንሳል:: ለወገን ሊቆሙ ታጥቀው የቆሙት ባለ ብዙ ብሶት ሐኪሞቻችንን አርፎ በመቀመጥ እንኩዋን ትብብር ብናደርግላቸው ይህን ያህል ትልቅ ነገር ነው?

አንተን አይገድልህ ይሆናል : የአንተ ንዝህላልነት ግን ሀገሪቱን ሽማግሌ አልባ ያደርጋታል:: ወጣትንም አይተውም:: ለወላጆቻችን ስንልም መጠንቀቅ እየቻልን “አባዬ እማዬ” ብንል ዋጋ የለውም:: ለመቀባበርም ጤና ያስፈልጋል:: መንግሥትም የየትኛውም ፓርቲ ደጋፊ ያልሆነ በሽታ መምጣቱን ተረድቶ አላስፈላጊ ስብሰባዎችን ማስቆም : ከምግብና ጤና ነክ ውጪ ያሉ የሥራ እንቅስቃሴዎችን ማስቆም ይገባዋል:: ሁኔታዎች ሳያስቆሙን እኛ ማቆም የምንችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ:: ለጥቂት ጊዜ መሸሸግ እጅግ መልካም ነው::

+ የኮሮና ሌላው ገጽታ +

በዚህ ወቅት በቤት ለመቆየት ለተገደዳችሁ ሁሉ! ነገም ለምትገደዱ ሁሉ! ሓላፊነት ተሰምቶአችሁ ከእንቅስቃሴ ለተገታችሁ ሁሉ በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት እነዚህን መልካም ዕድሎች አታሳልፉ እነዚህንም አስታውሱ

1. ንስሓ ዋነኛው ነው

ወደ እግዚአብሔር በንስሓ መቅረብ ከተጣሉት መታረቅ : የበደሉትን ይቅርታ መጠየቅ : የተቀየሙትን ይቅር ማለት ጊዜው አሁን ነው:: የማናናግራቸው የዘጋናቸውን ሰዎች እስቲ ዛሬ እናስባቸው:: በሞት ጥላ ተከብቦ የማይታረቅ የለምና ይህንን ጊዜ ለሰላም እናድርገው:: በንግግር ያቆሰልናቸውን በፍቅር ቃል እንካሳቸው:: ምሕረት የሚወርደውም በዚህ ነው::

2. መከራ የጸሎት ትምህርት ቤት ነው

በጨነቀኝ ጊዜ ሁሉ እግዚአብሔርን ጠራሁት ይላል ነቢዩ:: በደስታችን ጊዜ የምንረሳው ፈጣሪም “በመከራህ ቀን ጥራኝ እኔም እሰማሃለሁ” ይላል:: እርግጥ ነው ብዙዎቻችን ስለ ፈጣሪ የምናስበው በጭንቅ ቀን ነው:: እርሱ ግን የት ከርመህ ሲጨንቅህ አስታወስከኝ አይልም:: “እግዚአብሔር መልካም ነው በመከራ ቀንም መሸሸጊያ ነው”
ይህ ወቅት ጸሎት የምንማርበት ወቅት ነው:: በተለይ ውስጥን ጸጥ የሚያደርገውን መዝሙረ ዳዊት ለመጸለይ ጊዜው አሁን ነው:: ጊዜ የለኝም ብለን ያላነበብናቸውን መጻሕፍት ያልተማርናቸውን ትምህርቶች ያልሰራናቸውን የቤት ሥራዎች የምንሠራበት ወቅት ነው:

3 ከቤተሰብ ጋር ጊዜ ማሳለፊያ ወቅትም ነው

በሥራ በትምህርት በማኅበራዊ ሩጫ ምክንያት ቤተሰቦቻችንን የዘነጋን ብዙ ነን:: ልጆቻቸው የሚደውሉበትን ቀን በናፍቆት እየጠበቁ ስልካቸውን በጉጉት የሚያዩ : ከሰላምታ ባለፈ ቁጭ ብለን የማናናግራቸው : የሚሰማቸው ያጡ አያቶቻችን እናት አባቶቻችንን ቁጭ ብለን የምንሰማበትና የማይረሳ ጊዜ የምናሳልፍበት ጊዜ ይኼ ነው::

4. ይህ ጊዜ የምጽዋት ጊዜ ነው

በእንቅስቃሴ መገታት ምክንያት ብዙ ሥራዎች ይቆማሉ:: በሀብታሞቹ ሀገራት እንኩዋን ወደ ነበርንበት የዕለት ተዕለት ኑሮ ለመመለስ ቢያንስ አራት ወራት ያስፈልጋል እያሉ ነው::

ወዳጄ ዛሬ በእኛ ሀገር “ከቤት አትውጡ” ሲባል ቤት የሌላቸውም እንዳሉ አንዘንጋ:: ረሃብ ሳይመጣ ሸምቱ ሲባል ለዕለት ጉርስ ያጡ እና ራቴን ፈጣሪ ያውቃል የሚሉ ብዙዎች ናቸው:: እኛ ስለ ጉዋንትና አፍ መሸፈኛ በፋርማሲ ደጅ ተሰልፈን ስንጨቃጨቅ ምን እየተከናወነ እንደሆነ ግራ የሚገባቸው ዕርቃናቸውን መሸፈኛ ያጡ ብዙ ናቸው:: “በሳጥንህ ውስጥ ያስቀመጥካቸው የማትለብሳቸው ልብሶች የወንድምህ ልብሶች ናቸው” ይላል ቅዱስ አምብሮስ:: በዚህ ሰዓት ከመስገብገብ ለወገን ማሰብ የተሻለ ነው:: ከክፉ የሚድነውም የራሱን ደህንነት ብቻ የሚያስብ ሳይሆን እንደ ሰራፕታዋ መበለት”በማድጋ ካለው ከእፍኝ ዱቄት፥ በማሰሮም ካለው ከጥቂት ዘይት በቀር እንጀራ የለኝም፤ እነሆም፥ ገብቼ ለእኔና ለልጄ እጋግረው ዘንድ በልተነውም እንሞት ዘንድ ጥቂት እንጨት እሰበስባለሁ” ማለትና ለኤልያሶች እንጎቻ መጋገር የቻለ ነው:: ሁኔታዎች እስኪስተካከሉ ቢያንስ ወራት ይወስዳል:: በረሃብ ጊዜ ደግሞ መተዛዘን የግድ ያስፈልጋል::

“አቤቱ፥ በቍጣህ አትቅሠፈኝ፥ በመዓትህም አትገሥጸኝ” መዝ ፮፥ ፩

Posted in: መረጃ, ኮሮና ቫይረስ Tagged: A solution to Coronavirus, BC, Canada, Coronavirus, COVID-19, EOTC, Ethiopia, God is the solution, Holy Synod, how to treat COVID-19, Parish, Prayer is powerful, Return to God, Save me, The Orthodox way, Victoria

ቅዱስ ሲኖዶስ ያወጣው ዝርዝር መግለጫ ፪

March 23, 2020 by admin Leave a Comment

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የኖብል ኮሮና ቫይረስ በሰው ዘር ላይ የደቀነውን አስከፊ አደጋ በውል በማጤን ምእመናንን እና ሀገርን ከመከራ ለመጠበቅ በድጋሚ ዘርዘር ያለ መመሪያ አውጥቷል።

የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ 13ቱ ነጥቦች ቀጥሎ የተዘረዘሩት ናቸው።

  1. በሰሙነ ሕማማት እንደምናደርገው የእርስ በርስ መሳሳም ቀርቶ ራስን ዝቅ በማድረግ፣ እጅ በመንሳት ወይም በእማሄ ሰላምታ በማቅረብ እንዲፈጸም፣
  2. ወረርሽኙ በሰዎች መሰባሰብ የሚስፋፋ ስለሆነ ማናቸውም መንፈሳዊ ጉባኤያት፣ የትምህርት ክፍለ ጊዜያት፣ ወደ ገዳማትና አድባራት የሚደረጉ ጉዞዎች እና ምዕመናን የሚሳተፉባቸው ታላላቅ መርሐ ግብሮች ለጊዜው እንዲቋረጡ፣
  3. ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገባም ሆነ አሰፈላጊ በሆነበት ጊዜ ሁሉ እጆቻንን በመታጠብና ዘርዘር ብሎ በመቆም ሥርዓተ አምልኮ እንዲፈጸም፣
  4. ዓመታዊ የንግሥ ክብረ በዓላት በቅዳሴና በማኅሌት ታስበው ክብረ በዓላቱ በሌላ ጊዜ እንዲከበሩ፣
  5. የጉንፋን ምልክት ያለባቸው ለሌሎች እንዳያስተላልፉ በቤታቸው በጥንቃቄ ተለይተው በጸሎትና በሕክምና እንዲቆዩ፣ ከቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ አገልግሎትም በልዩ ሁኔታ እንዲያገኙ፣
  6. በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የተስፋ ልዑክ በመሆን እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ተደራጅቶ ተልዕኮውን በአስቸኳይ እንዲጀምር፣
  7. ሥርዓተ ቅዳሴን በተመለከተ፦
  • በቤተ መቅደስ ቀዳስያን በሆኑት ልዑካን ብቻ ሥርዓተ ቅዳሴው እንዲፈጸምና ሌሎች አገልጋዮች በቅድስቱ ዘርዘር ብለው በመቆም እንዲያገለግሉ፣
  • በዕለቱ ለሚቆርቡ ምዕመናን ለአረጋውያን፣ ለወጣቶችና ለሕፃናት የፈረቃ ተራ በማዘጋጀት ቆራቢዎች ብቻ ወደ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ገብተው ዘርዘር ብለው በመቆም እንዲያስቀድሱ፤
  • ሌሎች ምእመናን በአጸደ ቤተክርስቲያን ቢያንስ ሁለት የትልቅ ሰው እርምጃ ያህል በመራራቅ ቆመው እንዲያስቀድሱ፣
  • የቅዳሴ ጠበል በየግል መጠቀሚያ ምእመናን በየቆሙበት ቦታ በጥንቃቄ እንዲሰጥ፣
  • ሌሎች ከቅዳሴ ጋር የተያያዙ ዝርዝር የአፈፃፀም ጉዳዮችን ግብረ ኃይሉ አዘጋጅቶ በቅዱስ ሲኖዶስ በማጸደቅ ለአህጉረ ስብከት በሚልከው መመሪያ መሠረት ተግባራዊ እንዲደረግ፤

8. ከሥርዓተ ቅዳሴ በተጨማሪ እንደ ስብሐተ ነግሕ፣ ሰዓታት፣ ቁመተ ማኅሌት፣ ጥምቀተ ክርስትና፣ ጸሎተ ፍትሐት፣ የመሳሰሉ አገልግሎቶች ለሥርዓቱ በሚያስፈልገው ቁጥር ብቻ እና በውሱን ሊቃውንት በተራ እንዲፈፀም፣

9. ወረርሽኙ ከዓለም እንዲጠፋ ካህናት ብቻ በቤተ መቅደስ፣ በዐውደ ምኅረትና በአጸደ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ጸሎተ እጣን በማድረስ ማዕጠንት እንዲፈጽሙ፣

10. በማኅበራዊ ግንኙነት በደስታ፣ በሐዘን፣ በእድር፣ በሥርዓተ ቀብር አፈፃፀምና በመሳሰሉት መሰባሰቦች በሽታው እንዳይሠራጭ አገልግሎቱ በውስን የሰው ቁጥር በጥንቃቄ እንዲፈፀም፤

11. ምዕመናን ራሳቸውን እየጠበቁ በቫይረሱ የተጠቁና አገግመው የወጡ ወገኖችን፣ እንዲሁም በውጭ ሀገር ዜጎች ላይ ከሃይማኖትና ከምግባር የወጣ መገለልና ጥቃት እንዳይደርስባቸው በክርስቲያናዊ ፍቅርና በኢትጵያዊ ጨዋነት እንክብካቤ እንዲደረግላቸው፣

12. ለነዳያን እና ለተቸገሩ ወገኖች አስፈላጊው ማኅበራዊ እና ቁሳዊ እገዛ በሁሉም አጥቢያዎች እንዲደረግ፣

13. ቤተ ክርስቲያንን ከማይወክሉና ቀኖናዊ ካልሆኑ አሳሳች መረጃዎች በመቆጠብ ሊቃውንት፣ ካህናት፣ መምህራን፣ ሰባክያን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚሰጡ መመሪያዎችን በየአጥቢያችሁና አስፈላጊ በሆኑ ቦታዎች ሁሉ እንድትፈጽሙ እና እንድታስፈጽሙ ተወስኗል፡፡

Posted in: መረጃ, ኮሮና ቫይረስ Tagged: A solution to Coronavirus, BC, Be pleased, Canada, Coronavirus, COVID-19, EOTC, Ethiopia, God is the solution, Holy Synod, how to treat COVID-19, Lord, Parish, Prayer, Prayer is powerful, Return to God, Save me, The Orthodox way, Victoria, ሰበካ ጉባኤ, ቅዱስ ሲኖዶስ, ቅዱስ ቂርቆስ, አቡነ ሀብተ ማርያም, አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ

የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ፥ መጋቢት ፲፪

March 21, 2020 by admin Leave a Comment
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት እና መስፋፋትን ለመግታት በብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  ከቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊና የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የተሰጠ ማብራሪያ

በመላው ዓለም ለምትገኙ ወገኖቻችን በሙሉ!

የወቅቱ የዓለማችን ሥጋት በመሆን በፍጥነት እየተስፋፋ በሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት በርካታ ሀገሮች ብሔራዊ ሥጋት ስላደረባቸው እርምጃዎችን በመወሰድ ላይ ናቸው፡፡

በሽታውን እንዳይዛመት ከመከላከል ውጭ የሚፈውስ መድኀኒት ስለሌለው፣ በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው ስለሚዛመት፣ ጾታና የዕድሜ ክልል ሳይለይ ይልቁን አረጋውያንን ስለሚያጠቃ፣ ሁሉም ሀገሮች የመተላለፊያ መንገዶች በመለየት ሥርጭቱን ለመግታት ዝርዝር መግለጫ በማውጣት ሕዝባቸው ከሞት፣ ሀገራቸውን ከጥፋት ለመከላከል እየጣሩ ይገኛሉ፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ጸሎትና ምሕላ አጠናክሮ ከማድረግ በተጨማሪ ጤነኞችን የመጠበቅ፣ ሕሙማን የመንከባከብና የማጽናናት ኃላፊነት ስላለባት ቋሚ ሲኖዶስ ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፏል፡-

1. ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ጀምሮ በየደረጃው የሚዋቀር ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ከጤና ባለሙያዎች የተውጣጣ ግብር ኃይል ተቋቁሟል፤

2. ግብረ ኃይሉ ከሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር አስፈላጊ መረጃዎችን በማሰናዳት በቅዱስ ሲኖዶስ እያስወሰነ ተግባራዊ እንዲያደርግ፣

3. ከቤተ ክርስቲያን ቀኖና ጋር የማይጋጩ የመከላከያ መንገዶች ማለትም የእጅ ለእጅ መጨባበጥን ማቆም፣ እጅን በሚገባ መታጠብ፣ ሳይጠጋጉ ዘርዘር ብሎ መቆም፣ በመሳልና በማስነጠስ ጊዜ መጠንቀቅ፣ በመሳሳም ምትክ እማሄ ወይም ሰላምታ መስጠት በየአጥቢያው፣ በየገዳማቱና በያለንበት ሁሉ ተግባራዊ እንዲደረጉ፤

4. መንፈሣዊ የስብከተ ወንጌል ጉባኤያት፣ የመንፈሳዊ ጉዞ መርሐ ግብሮች ለጥቂት ቀናት እንዲቆሙ፣ በቅዳሴና በምሕላ ጸሎት ጊዜ በውስጥም ሆነ በአጸደ ቤተ ክርስቲያን ዘርዘር ብሎ በመቆም መንፈሳዊ አገልግሎቶችን እንዲፈጸሙ፣  

5. ሊቃውንት፣ ካህናት፣ መምህራን፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ ከተሳሳቱ መረጃዎች ተቆጥባችሁ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚሰጡ መመሪያዎችን በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑና አስፈላጊ በሆኑ ቦታዎች ሁሉ እንድታስፈጽሙ፣

6. ለራሳችንና ለወገኖቻችን በመቆርቆርና በመተዛዘን፣ አረጋውያንን በመጠበቅ፣ ነዳያን በማሰብ የበሽታውን ሥርጭት ተባብረን እንድናስቆም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ይኽንን አስከፊ በሽታ ከዓለማችን እንዲያጠፋልን በማያልቅ ቸርነቱና በቅድስት እናቱ ድንግል ማርያም አማላጅነት በምኅረቱና በይቅርታው ብዛት ይማረን፡፡

አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

የኢኦተቤ ቲቪ

Posted in: መረጃ, ኮሮና ቫይረስ Tagged: A solution to Coronavirus, BC, Be pleased, Canada, Coronavirus, COVID-19, EOTC, Ethiopia, God is the solution, Holy Synod, how to treat COVID-19, Lord, Parish, Prayer, Prayer is powerful, Return to God, Save me, The Orthodox way, Victoria, ሰበካ ጉባኤ, ቅዱስ ሲኖዶስ, ቅዱስ ቂርቆስ, አቡነ ሀብተ ማርያም, አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ, ኮሮናቫይረስ

ከሰበካ ጉባኤ የተሰጠ ማሳሰቢያ፥ መጋቢት ፲፪

March 21, 2020 by admin 1 Comment

የኮሮና ቫይረስን (COVID-19) አስመልክቶ ከሰበካ ጉባኤ የተሰጠ ማሳሰቢያ

“እናንተ ፍርዱን የጠበቃችሁ የምድር ትሑታን ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ፈልጉ፤ ጽድቅንም ፈልጉ፥ ትሕትናንም ፈልጉ፤ ምናልባት በእግዚአብሔር ቍጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል” ሶፈ ፪፥ ፫

እግዚአብሔር አምላክ በአሕዛብ ዘንድ ያለው ኃጢአት ከትዕግሥቱ ልክ በሚያልፍ ጊዜ ቁጣው ይበረታል፤ በሕዝቡ መካከል ያለውን ኃጢአትም አይታገሥም፡፡ አሕዛብም የእግዚአብሔርን ትዕግሥት እና የተሰጣቸውንም የንስሓ ዕድል እየገፉ፣ የባሰ ክፋት ሲሠሩ በእግዚአብሔር ቁጣ ሥር ይወድቃሉ “ስለዚህ ቍጣዬን አፈሰስሁባቸው፥ በመዓቴም እሳት አጠፋኋቸው፤ መንገዳቸውንም በራሳቸው ላይ መለስሁ” ይላል ጌታ እግዚአብሔር (ሕዝ. ፳፪፥ ፴፩) መዓት በሰው ልጅ ግብር ይመጣል፤ ምሕረት ደግሞ በእግዚአብሔር ቸርነት ይገኛል።

በዓለም ዙሩያ በሕክምናው ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎች ለበሽታው መድኃኒት በማጣታቸው መንግሥታት ለዜጎቻቸው ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አስጠንቅቀዋል፤ መከላከያ ሊሆኑ ይችላሉ የሚሏቸውን መንገዶች አስታውቀዋል፡፡ ቤተክርስቲያናችንም ሰዎች በክፉ ደዌ ሲያዙ ፈውሰ ሥጋን እንዲያገኙ ጸበል፤ ጾምና ጾሎት እንዲበዛ ታስተምራለች። እንዲሁም ለኃጢያት እስካልዋለ ድርስ ጥበብ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተሠጠ በመሆኑ ባለሙያዎች የሚሉንን መስማት የእግዚአብሔርን ጥበብ መስማት መሆኑን ልብ ልንል ይገባናል።

ቅዱስ ሲኖዶስ እስከ ትንሣኤ ድርስ ያወጀውን ምሕላ እያደረስን ሰርክ ሰንበት ለሚኖረው የቅዳሴ አገልግሎት የሚከተሉትን ማሳሰቢያዎች የሰበካ ጉባኤ አስተዳደር ማሰተላለፍ ይፈልጋል።

  1. የሰንበት ዝክርና ጸበል ጸዴቅ ከመጪው እሑድ ማርች 28 ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አይኖርም።
  2. ለቅዳሴ አገልግሎት ቆራቢ (ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን የሚቀበሉ) የሆኑ ብቻ በመቅደስ ውስጥ እንዲገቡና መቅደስ ውስጥም የተጠየቀውን ርቀት (ከ1-2 ሜትር) ተጠብቆ እንዲቆም እናሳስባለን።
  3. ወደ ታች (down stair) ለአገልግሎትና ለንጽህና ጉዳይ ካልሆነ በቀር ከደረጃው ጀምሮ የተዘጋ ይሆናል።
  4. የውስጡ ቦታ ከሞላ በአጽዱና ፊት ለፊት ተገቢ ርቀትን ጠብቆ እንድስታስቀድሱ እንጠይቃለን።
  5. የቅዳሜም ሆነ የሰንበት ምንም ዓይነት የሕጻናትና ታዳጊዎች መርሃግብር አይኖረንም (የውጭ ጨዋታን ጨምሮ)
  6. ወደፊት እግዚአብሔር በፈቀደልን መጠን የሰንበት ትምህርት ቤት መርሃግብሩን ወደ አየር ላይ ሥርዓት (online) ለማስተላለፍ እንዲሁም ቅዳሴውን በቀጥታ እንድትከታተሉ (live) ለማድረግ ወይም ሌሎች አማራጮችን የምናስተዋውቃችሁ ይሆናል።

የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ለምትፈልጉት ሁሉ አይቋረጥም። ለሚኖራችሁ ጥያቄዎች በስልክ፣ በኢሜይል ወይም ድረ ገጻችንን መጠቀም የምትችሉ መሆኑን እያሳወቅን ጊዜው ያለዕምነት የምናሳልፈው አይሆንምና ሁላችንም ወደ ተግባራዊ ክርስትና እንድንመጣ ለዚህም በጾምና ጸሎት ባለንበት በመበርታት እምነታችንን እንድናሳድግ እናሳስባለን። ወደ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር በመመለስ፣ ይቅርታና ምሕረትን በመለመንና ንስሓ በመግባት ቁጣውን ወደ ምሕረት እንዲለውጥልን መማጸን አለብን፡፡ ይህም በእግዚአብሔር ዓይን ቀላል ነው፤ ዳሩ ግና ድንገት መጥቶ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ፥ ጊዜው መቼ እንዲሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ ትጉ ጸልዩም ተብለናልና (ነገ ካል ፫፥ ፲፰፣ ማር ፲፫፥ ፴፫-፴፮)

ለበለጠና አበረታች መልዕክቶች ደብሩ ለዚህ ብሎ ያዘጋጀውን ድረ ገጽ በመከታተል ራሳችንን በእግዚአብሔር ቃል እናጠንክር።

የምህረት አምላክ እግዚአብሔር የመጣውን ቁጣ ያሳልፍልን፤ አገራችን ኢትዮጵያንም ይጠብቅልን

የሰበካው ጉባኤ አስተዳደር

Posted in: መረጃ, ኮሮና ቫይረስ Tagged: A solution to Coronavirus, BC, Be pleased, Canada, Coronavirus, COVID-19, EOTC, Ethiopia, God is the solution, how to treat COVID-19, Lord, Parish, Prayer, Prayer is powerful, Return to God, Save me, The Orthodox way, Victoria, ሰበካ ጉባኤ, ቅዱስ ቂርቆስ, አቡነ ሀብተ ማርያም, አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ, ኮሮናቫይረስ

አቤቱ እኔን ታድነኝ ዘንድ ውደድ

March 19, 2020 by admin Leave a Comment

በቅዳሴኣችን መግቢያ ላይ “በሃይማኖት በምግባር አንድ ነን” የሚለውን ለመግለጥ ሠራዒው ቄስ እጁን ከንፍቁ ቄስ ጋር በማገናኘት በተራክቦተ እድ (በመጨባበጥ) እንዲህ ሲል በትህትና ይለምነዋል

“ተዘከረኒ ኦ አቡየ ቀሲስ በጸሎትከ ቅድስት አባቴ ሆይ ክብርት በምትሆን በጸሎትህ አስበኝ” ያን ጊዜ መሓሪው አምላክ ከቀሳፊ መልአክ ይሠውርህ ፣ ከሹመትህ አይሻርህ ፣ መሥዋዕት ጸሎትህን በባለሟልነት ይቀበልልህ የሚለውን ምኞት “እግዚአብሔር ይዕቀባ ለክህነትከ ወይትወከፍ መሥዋዕትከ ወቊርባነከ በብሩህ ገጽ” ብሎ ንፍቁ ለዋናው ካህን ይመልስለታል፤

አያይዞም “አሐዱ…” ከማለቱ አስቀድሞ መላልሶ መጸለይ እንዲገባን ለማጠየቅ ፫ ጊዜ እየደጋገመ

✧ ሥመር እግዚኦ ከመ ታድኅኒ ⇝ ሥመር እግዚኦ ከመ ታድኅኒ ⇝ ሥመር እግዚኦ ከመ ታድኅኒ የሚለውን የዳዊት ቃል ይጸልያል። “አቤቱ፥ ታድነኝ ዘንድ ፍቀድ፤ አቤቱ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን።” መዝ. ፴፱ (፵)፥፲፫ [40፥13]

በእደ ኃጥኣን ተፈተትኩ ፣ በአፈ ረሲዓን ተወደስኩ ብሎ በረከቱን የማያስቀር ዛሬም የዕለተ ዓርቡን ሥጋና ደም እንደማያልቅ ንጹሕ ላህም እንደማያቋርጥ የእርድ በግዕ እውነተኛ መሥዋዕት አድርጎ የሚሰጠን እና የሚቀበለን ቸር አምላካችን ሕሙም “መፃጉዕ”ን በአያሌ የሥጋና የነፍስ ሕመምተኞች መኃል ለምናስብበት ፬ኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት እንኳን አደረሰን አደረሳችሁ!?

ይኽ ያዝነው ሳምንት የ፴፰ ዓመት ሕመምተኛ፣ በቀቢፀ ተስፋ የሚኖር በሽተኛ፣ ደዌ የጸናበት የአልጋ ቁራኛ… ወደ ሆነው መፃጉዕ ጌታችን ቀርቦ “ልትድን ትወዳለህን?” እንዳለው ዛሬ እኛ ግን ስለደረሰብን ጭንቅ ወደጌታችን ቀርበን “ልታድነኝ ትወዳለህን?” ብቻ ሳይሆ እንደ ልበ አምላክ ቅዱስ ነቢይና ንጉሥ ዳዊት “አቤቱ እኔን ታድነኝ ዘንድ ውደድ” እያልን ልንማፀን የሚገባበት ወቅት ነው!

በቅዱስ ሚካኤል ድርሳን በምናገኘው መርገፍ የእኛ የሆነው የሰው ልጆች ረዳት ቅዱስ ሚካኤል ከመጣብን ቁጣ ከደረሰብን ጭንቅ ያድነንና ያማልደን ዘንድ እንዲህ ብለን የአምላኩን ምሕረት ደጅ የምንጠናበትም ወቅት ነው!

ሚካኤል ኀቤከ አወዩ በአስተብቍዖ፣ ከመ ታድኅነኒ ሥመር እግዚኦ፣ እስመ ኩሉ ይተግህ ከመ ያድኅን ሰብኦ፤ [ሚካኤል ሆይ ለምልጃ ወደ አንተ እጮሃለሁ፡ አቤቱ ታማልደኝ ታድነኝ ዘንድ ፍቀድልኝ፡ ሰው ሁሉ የራሱን ለማዳን ይተጋልና።]

እግረ መንገድ አበው “ሥመር እግዚኦ” ሲሉት መጨባበጣቸውን ስናነሳ ከወቅቱ ጉዳይ ጋር “እደ ካህን”፣ ወንጌል፣ የአብያተ ክርስቲያን አፀድ አምድና አንቀጽ እንዲሁም መስቀልን መሳለም የአያሌዎች ሥጋትና ጥያቄ ሆኖ ቀርቧል!

በእርግጥ በመንፈሳዊ ቦታ የሚካሔዱ መንፈሳዊ ተግባራት መንፈሳዊ እምነትና ሃይማኖታዊ ዕይታን ብቻ በእጅጉ የሚጠይቁ ናቸው! ሳይንሳዊው ምልከታ ሥጋዊው እይታ ሚዛናዊ ምልከታን ለማስቀመጥ የሚጥር ነውና ከእምነት ጋር ማገናዘቡ አድካሚ ነው!

 እምነታችሁም በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን፥ ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበረ እንጂ፥ በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም (፩ኛ ቆሮ ፪፥፬-፭ )

መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን እንጂ የሰው ጥበብ በሚያስተምረን ቃል አይደለም (፩ኛ ቆሮ ፪፥፲፫)

የህክምና ማሳሰቢያና እምነት

ዝርዝሩን ያንብቡ [Read more…]

Posted in: መረጃ, ኮሮና ቫይረስ Tagged: A solution to Coronavirus, BC, Be pleased, Canada, Coronavirus, COVID-19, EOTC, Ethiopia, God is the solution, how to treat COVID-19, Lord, Prayer, Prayer is powerful, Return to God, Save me, The Orthodox way, Victoria, ቅዱስ ቂርቆስ, አቡነ ሀብተ ማርያም, አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ, ኮሮናቫይረስ

ከኮሮና ቫይረስ እንዴት እንጠበቅ?

March 18, 2020 by admin Leave a Comment

የሰማዕታቱ ቅዱስ ቂርቆስና ቅድስት ኢየሉጣ ስዕል

በዓለም ላይ የሚነሡት አብዛኞቹ ተላላፊ በሽታዎች በቅዱስ መጽሐፍ የተከለከሉት እንስሳትን፣ አራዊትንና አዕዋፍን በመመገብ የመጡ እንደሆኑ፤ እነርሱንም በድናቸውን የነካ እንዴት በሽታው እንደሚተላለፍበት በሽታውን ለማስወገድ ምን ማድረግ እንደሚቻል የንጽሕናውን ሂደት ሁሉ በዝርዝር ከመጋቢ ሐዲስ ሮዳስ “መጽሐፍ ቅዱስና የሕክምና ሳይንስ” ከሚለው መጽሐፍ ላይ በስፋትና በጥልቀት ማንበብ ይቻላል። በዚያ ላይ ያልተካተቱ ተላላፊ በሽታዎች ሲከሠቱ አባቶቻችን ምን ያደርጉ እንደነበር በተወሰነ መልኩ በጥቂቱ ከዚህ በታች ቀርቧል፡፡

፩. ካህናት በጸሎተ ዕጣን የማዕጠንት አግልግሎት መስጠት

ዳዊት አባታችን በመዝ ፻፵፥ ፪ “ተወከፍ ጸሎትየ ከመ ዕጣን በቅድሜከ” (ጸሎቴን በፊትህ እንደ ዕጣን ተቀበልልኝ) እንዳለ እግዚአብሔር ወዶ የሚቀበለው ጸሎተ ዕጣን ተላላፊ በሽታና መቅሠፍት በማራቅ ይታወቃል፡፡ ይኸውም በኃጢአታቸው ልዑል እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ሊቀሥፋቸው መቅሠፍቱ በጀመረና ሞት በመጣ ጊዜ ሙሴም አሮንን፦

“ጥናህን ውሰድ፥ ከመሠዊያውም ላይ እሳት አድርግበት፥ ዕጣንም ጨምርበት፥ ወደ ማኅበሩም ፈጥነህ ውሰደው አስተስርይላቸውም ከእግዚአብሔር ፊት ቍጣ ወጥቶአልና መቅሠፍት ጀምሮአል አለው፤ አሮንም ሙሴ እንደ ተናገረው ጥናውን ወስዶ ወደ ጉባኤው መካከል ሮጠ እነሆም፥ መቅሠፍቱ በሕዝቡ መካከል ጀምሮ ነበር ዕጣንም ጨመረ፥ ለሕዝቡም አስተሰረየላቸው፤ በሙታንና በሕያዋን መካከል ቆመ መቅሠፍቱም ተከለከለ” ይለናል፡፡ (ዘኁ ፲፮፥ ፵፰)

ዛሬም በመልአኩ እጅ ይህ የቅዱሳን ካህናት የዕጣን ጸሎት የሚያርግና ግዳጅ የሚፈጽም በመሆኑ አበው ካህናት ልብሰ ተክህኖ ለብሰው ማዕጠንታቸውን ይዘው ሀገሪቱን በማጠን በጸሎተ ማዕጠንት መንፈሳዊ አደራቸውን ሊወጡ ይገባቸዋል፡፡ በኅዳር በሽታ ጊዜ ሕዝቡ ቆሻሻውን ሲያቃጥል ካህናት በማዕጠንት ባጠኑት ዕጣን ተላላፊው በሽታ ተገትቷል፡፡ ይኸውም ኅዳር ሲታጠን ተብሎ አሁን ድረስ በታሪክ ይነሣል፡፡

በተለይ ጻድቁ አቡነ ሀብተ ማርያም ተላላፊ በሽታን በማዕጠንት ለማራቅ በዚህ ቃል ኪዳን የተሰጣቸው በመሆኑ የገዳሙ አባቶች በሀገራችን በተለያየ ስፍራ ተላላፊ በሽታ ሲመጣ የማዕጠንት አግልግሎት ሲሰጡ በሽታው እንደሚቆም ይታወቃልና መጠቀም የእኛ ድርሻ ነው፡፡

፪. በቤተ ክርስቲያን ተገኝቶ በምሕላ ወደ እግዚአብሔርን መጮህ

በምሕላና በጸሎት ተላላፊ በሽታ እንደሚወገድ ራሱ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስን ሠርቶ ለጨረሰው ለሰሎሞን ቃል ኪዳንን እንዲህ ገብቶለታል፡-

“ዝናብ እንዳይወርድ ሰማያቱን ብዘጋ፥ ወይም ምድሪቱን ይበላ ዘንድ አንበጣን ባዝዘው፥ ወይም በሕዝብ ላይ ቸነፈር (ተላላፊ በሽታ) ብሰድድ በስሜ የተጠሩት ሕዝቤ ሰውነታቸውን አዋርደው ቢጸልዩ፥ ፊቴንም ቢፈልጉ፥ ከክፉ መንገዳቸውም ቢመለሱ፥ በሰማይ ሆኜ እሰማለሁ፥ ኃጢአታቸውንም ይቅር እላለሁ፥ ምድራቸውንም እፈውሳለሁ” ይላል (፪ኛ ዜና ፯፥ ፲፫፥ ፲፬)፡፡

በመሆኑም ጦርነት፣ ተላላፊ በሽታ የመሳሰለው እንዲህ ዓይነት መከራ ጥንት ሀገር ሲያጋጥማት ነገሥታቱ ከካህናት ጋር በመማከር በአንድ ላይ ምሕላና ጸሎት በሀገሩ ሁሉ ባሉ በየገዳማቱና በየአድባራቱ ሁሉ ሥዕለ ማርያም ምስለ ፍቁር ወልዳ ወጥቶ በዕንባ ይደርስ ነበር፡፡ ዛሬም ይህንን ታላቅ የምሕላ ጸሎት በማድረስ የሚታወቁት በአክሱምና በጎንደር ነውና በመላዋ ሀገሪቱ ሊሆን ይገባል፡፡

ለምሳሌ ያህል አሁን በመጣው የኮሮና ወረርሽኝ ከኃያላን ሀገራት ውስጥ የአሜሪካ መራሔ መንግሥት ዶናልድ ትራምፕ ከትላንት ወዲያ መጋቢት ፮ በሰንበት እለት እንዲሁም ከአፍሪካ የኬኒያ መራሔ መንግስት ኡሁሩ ኬኒያታ ዛሬ መጋቢት ፰ ማክሰኞ ሀገር ዐቀፍ የጸሎት ቀን እንዲሆን አውጀዋል። አቶ ትራምፕ እንዳሉት “We are a Country that, throughout our history, has looked to God for protection and strength in times like these…. ….No matter where you may be, I encourage you to turn towards prayer in an act of faith. Together, we will easily PREVAIL!” (በታሪካችን ሁሉ እንደዚህ አይነት ፈተናዎች ባጋጠሙን ጊዜ እግዚአብሔር እንዲጠብቀንና እንዲያጠነክረን ለምነንዋል። ባላችሁበት ሁሉ በእምነት ጸልዩ በጋራም ቀላል ሆኖን እንወጣዋለን።) የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል። ዝርዝሩን ያንብቡ [Read more…]

Posted in: መረጃ, ኮሮና ቫይረስ Tagged: A solution to Coronavirus, BC, Canada, Coronavirus, COVID-19, Donald, EOTC, Ethiopia, God is the solution, how to treat COVID-19, Kenyatta, Prayer, Prayer is powerful, Return to God, The Orthodox way, Trump, Uhuru, Victoria, ቅዱስ ቂርቆስ, አቡነ ሀብተ ማርያም, አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ, ኮሮናቫይረስ

Coronavirus Disease 2019 (COVID-19) Global Map

March 15, 2020 by admin Leave a Comment

Global case numbers are reported by the World Health Organization (WHO) in their coronavirus disease 2019 (COVID-19) situation report.

Do you want to see locations with Confirmed COVID-19 Cases? Following the World Map link by WHO Region.

  • For Canada information, visit CDC’s COVID-19 in Canada
  • For BC information, visit CDC’s COVID-19 in BC
  • For Ethiopia information, visit EPHI’s COVID-19 in Ethiopia
  • For Eritrea information, visit MOH’s (at shabait news) COVID-19 in Eritrea
  • For U.S. information, visit CDC’s COVID-19 in the U.S.
Posted in: መረጃ, ኮሮና ቫይረስ Tagged: BC, Canada, Coronavirus, COVID-19, Eritrea, Ethiopia, Globalmap, U.S., Worldmap

ይህም በእግዚአብሔር ዓይን ቀላል ነው፤ ዳሩ ግና ድንገት መጥቶ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ፥ ጊዜው መቼ እንዲሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ ትጉ ጸልዩም (ነገ ካል ፫፥ ፲፰፣ ማር ፲፫፥ ፴፫-፴፮)

March 14, 2020 by admin Leave a Comment

🛑 ለጥንቃቄ🛑

በውሃን ቻይና ስለተገኘው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ምንነት፣ እንዴት ከሰው ወደ ሰው እንደሚተላለፍ እንዴት በዕለት ተዕለት የህይወት እርምጃ ውስጥ የቫይረሱን ስርጭት ማስቆም እንደሚቻል የተቀናበረ መረጃ!
©ዶ/ር ቤዛ አያሌው (ለብዙው ትንታኔ ምንጭ)

የዓለም ጤና ድርጅት የኮሮና ቫይረስ ዐለም አቀፍ ወረርሽኝ እንደሆነ አውጇል። ስለሆነም ቫይረሱ እስካሁን ያልተገኘባቸውም ሀገራት አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

መግቢያ

  • ኮሮና ቫይረስ የአፍንጫ እርጥበት እና አክታ የሚያስከትል ሳል ያለው አይደለም፡፡ በተቃራኒው አፍንጫ የማያረጥብ እና ደረቅ ሳል የሚያስከትል በመሆኑ በቀላሉ ልንረዳው የምንችለው ነው፡፡
  • ቫይረሱ ከ26-27 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ያለውን ሙቀት መቋቋም የማይችል በመሆኑ ይሞታል፡፡ ስለዚህ እንደ ሻይ፣ ሾርባ ፣ ትኩስ ውሃ..ወዘተ ያለትን ትኩስ ነገሮች በየቀኑ ደጋግሞ መጠጣት ቫይረሱንይገድበዋል፡፡ ትኩስ ነገሮችን መጠጣት ደግሞ ከባድ አይደለም፡፡
  • በጣም የቀዘቀዘ ውሃ አትጠጡ፣ የበረዶ ኩቦችን (ice cube) ወይም አመዳይ (snow) አትመገቡ!
  • የምትችሉ ሁሉ የጸሐይ ሙቀት ተቀበሉ፡፡

የሚተላለፍበት መንገድ

1. ኮሮና ቫይረስ ከ400-500 ናኖሜትር ዳያሜትር ርዝመት ያለው ትልቅ ቫይረስ በመሆኑ ለመከላከል የሚያስፈልገው ጭምብል ወይም ማስክ በተለየ መንገድ የተሰራ መሆን የለበትም፡፡ ማንኛውንም አይነት ጭምብል መጠቀም ይቻላል፡፡
  • በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች በሚገኙባቸው ተቋማት የሚያክሙ የጤና ባለሙያዎች ግን የተለዩ የመከላከያ መንገዶችን መጠቀም አለባቸው::
  • አንድ በቫይረሱ የተጠቃ ሰው ከፊት ለፊታችሁ ከ3 ሜትር ርቀት ላይ ቢያስነጥስ ቫይረሶቹ ወደ ምድር የሚወድቁ በመሆናቸው በቫይረሱ ተጠቂ አትሆኑም፡፡
2. ቫይረሱ ብረትነት ባላቸው ገጾች/አካሎች ላይ ካረፈ በኋላ ለ12 ሠዓታት በህይወት ሊኖር ይችላል፡፡ ስለዚህ ከብረት የተሰሩ እንደ እጀታዎች፣ በሮች፣ የቤት ዕቃዎችን፣ የአውቶቡስ የባቡር ወይም የትራም መደገፊያ እጀታዎችን ወይም ምሰሶዎችን ከነካችሁ በኋላ እጃችሁን በደምብ በሳሙና መታጠብ ይገባል፡፡
3. ቫይረሱ በልብስ እና በጨርቆች ውስጥ ተሰግስጎ ከ6-12 ሰዓታት ሊኖር ይችላል፡፡ ስለዚህ መታጠብ የሚችሉትን ልብሶች በሙሉ ዘወትር በምንጠቀምባቸው ሳሙናዎች ብናጥባቸው ቫይረሱን ይገድለዋል፡፡ በየእለቱ መታጠብ የማይችሉ ልብሶችን ጸሐይ ላይ ብታሰጡዓቸው ቫይረሱን የጸሐይ ሙቀት ይገድለዋል፡፡

ዝርዝሩን ያንብቡ [Read more…]

Posted in: መረጃ, ኮሮና ቫይረስ Tagged: BC, Canada, Coronavirus, COVID-19, Ethiopia, information, update, ማስታወቂያ, ማስጠንቀቂያ, ኮሮናቫይረስ

Public notice on #2019nCoV

January 30, 2020 by admin Leave a Comment

Public notice on #2019nCoV from @CDCofBC

There are several misconceptions on social media currently around how #coronavirus is transmitted. Please allow us to clear it up. #2019nCoV

  1. Receptors for #coronavirus are deep in a person’s lungs – a person must inhale enough of the virus that it can actually bind to those receptors deep in the lungs. 
  2. #Coronavirus is transmitted via larger droplets that fall quickly out of the air (for example, after a sneeze). This virus is not airborne.
  3. #Coronavirus is not something that people can get from casual contact. A person must be in close contact (within 2 metres) with somebody to be able to inhale those droplets if a person coughs or sneezes without cover, in front of them.
  4. The droplets can fall to the ground after a sneeze and a person can touch them with their hands. The risk of transmission is low in this case, as those droplets must be of significant enough quantity to make it to the receptors in a person’s lungs.
  5. If a person has touched something that has droplets on it with #coronavirus in it, as long as they clean their hands before touching their face or your mouth, they are not at risk of getting that virus in their body.
  6. #Coronavirus is not something that comes in through the skin. This virus is remitted through large droplets that are breathed deep into a person’s lungs.
  7. Regarding wearing masks – masks should be used by sick people to prevent transmission to other people. A mask will help keep a person’s droplets in.
  8. It may be less effective to wear a mask in the community when a person is not sick themselves. Masks may give a person a false sense of security & are likely to increase the number of times a person will touch their own face – to adjust the mask, etc.
  9. The most important thing that a person can do to prevent themselves from getting #coronavirus is to wash their hands regularly and avoid touching their face.
  10. Cover your mouth when you cough so you’re not exposing other people. If you are sick yourself, stay away from others. Contact your health care provider ahead of time so you can be safely assessed.
  11. Lots of questions whether #coronavirus can be spread through the eyes, nose and throat. Answer is YES! Virus is transmitted via larger droplets. If they come into contact with your eyes or are inhaled into your mouth or nose, they can enter from there too.

 

Posted in: መረጃ, ኮሮና ቫይረስ Tagged: BC, Canada, Coronavirus, COVID-19, Ethiopia, socialmedia, መረጃ, ኮሮናቫይረስ
1 2 Next »

BC’s Responses

Get COVID-19 Provincial Support

Public Health Officer Orders & Notices

Acess COVID-19 Self-Assessment Tool

More information from Health Link BC

COVID-19 Frequently Asked Questions (FAQS)

Canada’s Responses

Canada’s COVID-19 Economic Response Plan

Federal Public Health Notices

Provincial and territorial resources for COVID-19

More information from Public Health Canada

Recent Posts

  • የኮሮና ቫይረስን (COVID-19) አስመልክቶ ከሰበካ ጉባኤ የተሰጠ ማሳሰቢያ ሰኔ ፲፮
  • የኮሮና ቫይረስን (COVID-19) አስመልክቶ ከሰበካ ጉባኤ የተሰጠ ማሳሰቢያ ፪
  • የቋሚ ሲኖዶስ መግለጫ ፫
  • ብንሞትም ብንኖርም ለእግዚአብሔር
  • በኮሮና ዋዜማ

Recent Comments

  • help me write an essay on ከሰበካ ጉባኤ የተሰጠ ማሳሰቢያ፥ መጋቢት ፲፪
  • Selam on ብንሞትም ብንኖርም ለእግዚአብሔር

Categories

  • መረጃ
  • ኮሮና ቫይረስ

Meta

  • Log in
  • Entries feed
  • Comments feed
  • WordPress.org

Tags

A solution to Coronavirus BC Be pleased Canada Coronavirus COVID-19 Donald EOTC Eritrea Ethiopia Globalmap God is the solution Holy Synod how to treat COVID-19 information Kenyatta Lord Parish Prayer Prayer is powerful Return to God Save me socialmedia The Orthodox way Trump U.S. Uhuru update Victoria Worldmap መረጃ ማስታወቂያ ማስጠንቀቂያ ምን እናድርግ ሰበካ ጉባኤ ቅዱስ ሲኖዶስ ቅዱስ ቂርቆስ አቡነ ሀብተ ማርያም አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ኮሮናቫይረስ

Copyright © 2022 የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን St. Gabriel Church.

Church WordPress Theme by themehall.com