በዓለ ክብሩ ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል
እሑድ ታኅሳስ ፲፱, December 29, 2019 ከ2:00 AM እስከ 12:00 PM
በቪክቶሪያ መንበረ ብርሃን ዳግማዊ ቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን
1100 colville Road Victoria, BC V9A 4P7 (map)
ነቢዩ ዳንኤል “ዐይኖቼንም አነሣሁ” አለና አስከትሎ “እነሆም በፍታ የለበሰውን ጥሩም የአፌዝን ወርቅ በወገቡ ላይ የታጠቀውን ሰው አየሁ፡፡ አካሉም እንደ ቢረሌ ይመስል ነበር፤ ፊቱም እንደ መብረቅ አምሳያ ነበረ፤ ዐይኖቹም እንደሚንበለበል ፋና፣ ክንዶቹና እግሮቹም እንደ ጋለ ናስ፣ የቃሉም ድምፅ እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ ነበረ፡፡… ይህንም ታላቅ ራእይ አየሁ፤ ኀይልም አልቀረልኝም፤ ክብሬም ወደ ውርደት ተለወጠብኝ ኀይልም አጣሁ፡፡ የቃሉንም ድምፅ ሰማሁ፤ የቃሉን ድምፅ በሰማሁ ጊዜ ደንግጬ በምደር ላይ በግምባሬ ተደፋሁ” አለ፡፡ (ዳን.፲፥ ፭-፱)
ነቢዩ ዳንኤል እንዲህ ብሎ የተናገረው የመላእክት አለቃ የቅዱስ ገብርኤልን አስፈሪ ግርማ በተመለከተ ጊዜ ነበር፡፡ ቅዱስ ገብርኤል በብሉይ ኪዳን በቅድስና ሕይወት ለተጋውና በገዢዎች ዘንድ የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ ያደረበት ሰው (ዳን ፭፥፲11)ተብሎ ለተመሰገነው ለነቢዩ ዳንኤል ማስተዋልንና ጥበብን የሰጠ መልአክ ነበር፡፡ ለዚህ ነቢይ እግዚአብሔር አምላክ የሰው ልጆችን ከሰይጣንና ከሞት ባርነት ነጻ ሊያወጣቸው ሰው እንደሚሆንና ሰማይንና ምድርን አሳልፎ በቅዱሳን ላይ ነግሦ እንደሚኖር በምሳሌ ገልጾ ያስተማረው መልአክ ነው፡፡(ዳን ፱፥ ፳፩-፳፪) አሁንም ነቢዩ ዳዊት “አቤቱ እርዳታው ከአንተ ዘንድ የሆነለት በልቡም የላይኛውን መንገድ የሚያስብ ሰው ብፁዕ ነው፡፡ በልቅሶ ሸለቆ በወሰንኸቸው ስፍራ የሕግ መምህር በረከትን ይሰጣልና፡፡”(መዝ ፹፫፥ ፭-፮) እንዳለው በቅድስና ሕይወት በመጽናታቸው ምክንያት ቅዱስ ገብርኤል መምህር የሆናቸው ቅዱሳን ብዙዎች ናቸው፡፡ የእኛ እውቀት በሰማያት ከትመው ካሉት ቅዱሳን መላእክት እውቀት ጋር ሲነጻጸር እኛን እንደ ሕፃናት ያደርገናል፡፡ እኛ የእነርሱን እውቀት ገንዘባችን የምናደርገው በትንሣኤ ነው፡፡
ሶስቱ ሕጻናቶች
ቅዱስ ገብርኤል ቅዱሳን ይሆኑ ዘንድ ለተጠሩት መንፈሳዊ እውቀቱን የሚያካፍላቸው መልአክ ብቻ አይደለም፤ ለእግዚአብሔር በመገዛታቸው ምክንያት ከአላውያን ገዢዎች ከሚደርስባቸው መከራም የሚታደጋቸው መልአክም ነው፡፡ የፋርስ ንጉሥ የነበረው ናብከደነፆር እግዚአብሔር አምላክ ምድሪቱን ሁሉ ሲያስገዛለት በትዕቢት ተሞልቶ “በኃይሌ አደርጋለሁ፣ በማስተዋል ጥበቤም የአሕዛብን ድንበሮች አርቃለሁ፣ ሀብታቸውንም እዘርፋለሁ፣ የሚቀመጡባቸውንም ከተሞች አናውጣለሁ፣ በእጄም ዓለምን ሁሉ እንደ ወፍ ቤት እሰበስባለሁ፣ እንደ ተተወ እንቁላልም አወስዳቸዋለሁ፤ከእኔም የሚያመልጥ የለም የሚቃወመኝም የለም፡፡”(ኢሳ ፲፥ ፲፫-፲፬) ብሎ በመታበይ የወርቅ ጣዖትን አሠርቶ ዱራ(አዱራን) በሚባል ስፍራ ላይ አቆመው፡፡ በግዛቱ በልዩ ልዩ የሥልጣን እርከን ላይ ያሉትን ሹማምንቱንና ገዢዎችን ሰበሰባቸው፤ “የመለከትና የእንቢልታ የመሰንቆና የክራር የበገናና የዋሽንትን የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ወድቃችሁ ንጉሥ ናብከደነፆር ላቆመው ለወርቁ ምስል ስገዱ፡፡ ወድቆም ለማይሰግድ በዚያን ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣል” ብሎ አዋጅ አስነገረ፡፡ ይህን አዋጅ የሰሙ የንጉሥ ሹማምንት ሁሉ የመለከቱና የእንቢልታው እንዲህም የዘፈን ድምፅ በተሰማ ጊዜ ተደፍተው ለወርቁ ምስል ሰገዱ፡፡
በባቢሎን አውራጃዎች ላይ የተሾሙ አዛርያ(ሲድራቅ)፣ አናንያና(ሚሳቅ) ሚሳኤል(አብደናጎ) ግን ንጉሥ ላቆመው ምስል አልሰገዱም፡፡ ነገር ሠሪዎችም ይህንን ወሬ ለንጉሥ ነገሩት፤ ንጉሥም እጅግ ተቆጥቶ ወደ እርሱ አስጠራቸው፡፡ እርሱ ላቆመው ለወርቅ ምስል ያልሰገዱ እንደሆነ እጅና እግራቸውን ታስረው ወደ እቶን እሳቱ እንደሚጣሉ አስጠነቀቃቸው፡፡ ሠልስቱ ደቂቅ ግን “ናብከደነፆር ሆይ! በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አንፈልግም፡፡ ንጉሥ ሆይ! እኛ የምናመልከው አምላክ በሰማይ አለ፣ ከሚነደውም ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፤ ንጉሥ ሆይ! ይህም ባይሆን አማልክትህን አንዳናመልክ፣ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ” ብለው መለሱለት፡፡ የንጉሥ ናብከደነፆር ቁጣ ከፊት ይልቅ እጅግ ነደደ እሳቱንም ሰባት እጥፍ እንዲያቀጣጥሉና እነዚህን ሦስት ብላቴኖች እጅና እግራቸውን አስረው ከእነ ማዕረግ ልብሳቸው ከእቶን እሳት ውስጥ እንዲጨምሩአቸው ትእዛዝን አስተላለፈ፡፡ ትእዛዙ አስቸኳይ ነበርና እነርሱን ወደ እሳቱ የጣሏቸውም ኃያላን በእሳቱ ወላፈን ተገርፈው ሞቱ፡፡ እንዲህ ሲሆን ሳለ ግን ሠልስቱ ደቂቅ ወደ አምላካቸው “በፍጹም ልባችን እናምንሃለን፣ እንፈራሃለን፣ አታሳፍረን እንጂ ገጸ ረድኤትህንም እንፈልጋለን፡፡” እያሉ ይጸልዩ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ጸሎታቸውን ተቀበለ፤ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልንም ከመጣባቸው መከራ ይታደጋቸው ዘንድ ላከው፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም እስራታቸውን ፈታ፤ እሳቱን እንደ ውኃ አቀዘቀዘው፡፡ ሠልስቱ ደቂቅም መልአኩን ልኮ ከዚህ እቶን እሳት ያዳናቸውን አምላክ “የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይክበር ስምህም ለዘለዓለም የተመሰገነና የከበረ ነው” በማለት አመሰገኑት፡፡
ንጉሥ ናብከደነፆርም ሠልስቱ ደቂቅ እሳቱ አንዳች ጉዳት ሳያደርስባቸው በእሳት ውስጥ ሲመላለሱ ከእነርሱ ጋር የሰው መልክ ያለው ነገር ግን አምላክን የሚመስል መልአክ ተመለከተ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ሊቀ ካህናቱን ቀያፋን ፊቱን ጸፍቶ አፉን ከፍቶ “ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለሕዝቡ ይሞት ዘንድ እንዲሻለን አታስቡምን”(ዮሐ ፲፩፥ ፵፱) ብሎ እንዳናገረው እንዲሁ ናብከደነፆርንም “እነሆ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎችን በዚያ አያለሁ ምንም የነካቸው የለም፤የአራተኛውም መልክ የእግዚአብሔርን ልጅ ይመስላል” ብሎ እንዲናገር አደረገው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅን መልክ ያለው ያለው በኋላም መልአክ ብሎ የተናገረለት ቅዱስ ገብርኤልን ነበር፡፡ እርሱ ስለመሆኑ ለነቢዩ ዳንኤል በተገለጠበት ግርማ ማረጋገጥ እንችላለን፡፡
ናብከደነፆርም ወደ እሳቱ እቶን በመቅረብ እነዚህ ብላቴኖችን “እናንተ የልዑል አምላክ ባሮች ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም ኑ ውጡ ብሎ ተናገራቸው፡፡” እነርሱም ከእሳቱ ወጡ ሹማምንቱና መኳንንቱ፣ አማካሪዎችና የአገር ገዢዎች ሁሉ እሳቱ በእነዚህ ብላቴኖች ላይ አንዳች አቅም እንዳልነበረው፣ ከጠጉራቸው ቅንጣት አንዱን እንኳ እንዳላቃጠለው፣ ሰናፊናቸውም እንዳልተለወጠ፣ የእሳቱም ሽታ እንዳልደረሰባቸው ተመለከቱ፡፡ ንጉሥ ናብከደነፆርም መልአኩን ልኮ ያዳናቸውን የእነዚህን ቅዱሳንን አምላክ አመሰገነ፡፡ በእነርሱ አምላክ ላይም የስድብን ቃል የሚናገር ሰው እንደሚገደልና ቤቱም የጉድፍ መጣያ እንዲሆን አዋጅ አስነገረ፡፡ አዛርያ አናንያ ሚሳኤልም በንጉሡና በሹማምነቱ ዘንድ ሞገስ አገኙ በክብርም ከፍ ከፍ አሉ፡፡(ዳን ፫ በሙሉ)
ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን መንጎቹዋ የእምነትን ፍሬ ከእነዚህ ብላቴኖች ተምረው እግዚአብሔርን በማምለክ እንዲጸኑና የመልአኩን የቅዱስ ገብርኤልን ተራዳኢነት እንዲረዱ በታኅሣሥ ፲፱ ቀን ይህን ዕለት ትዘክራለች፤ በታላቅ ድምቀትም ታከብረዋለች፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እምነት በድርጊት ሊታይ የሚገባው ክርስቲያናዊ ተግባር ነው፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ አምናለሁ የሚል ሁሉ ካመነበት ጊዜ አንስቶ ክርስቶስን መስሎ ለመኖር ሊተጋና መስሎ ሊመላለስ ይገባዋል፡፡ በሠልስቱ ደቂቅ የታየው እምነት በአንድ ጀምበር የተገነባ እምነት ሳይሆን ከልጅነታቸው ጀምሮ በአንድ እግዚአብሔር ታምነው በቅድስና ሕይወት በመመላለስ የመጣ እምነት ነው፡፡ እነዚህ ብላቴኖች በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያገኙትን የድል አክሊል ተስፋ አድርገዋልና አርባ ዘጠኝ ክንድ ያህል የነደደውን የእሳት እቶን አላስፈራቸውም፤ በእግዚአብሔር ላይ ያላቸው ጽኑ እምነት በእሳት ተቃጥለው ለመሞት እንኳ አስጨከናቸው፡፡ እንዲህም ሆነው በመገኘታቸው በእምነታቸው እግዚአብሔርን ደስ አሰኙት፤ ስለዚህም እግዚአብሔር ባለሟሉን ቅዱስ ገብርኤልን በመላክ ከእሳቱ እቶን ታደጋቸው፡፡
የመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ምልጃና ጸሎት ይጠብቀን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!